የቀድሞ የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ለገሰ ሐንቆሬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ
አቶ ለገሰ ሐንቆሬ ከአባታቸው ከአቶ ሐንቆሬ ቦንግዶ እና ከእናታቸው ወ/ሮ ላሎቴ ወአጎ በቀድሞ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት ከምባታ ሀዲያ አውራጃ ኦሞ ሸለቆ: በአሁኑ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ ልዩ ስሙ ቤሌላ በሚባል አካባቢ በ1947 ዓ.ም ተወለዱ።
እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአካባቢው በሚገኙ በአምቡኩና አድቬንትስት፣ ሶያሜ የወንጌል አማኞች ትምህርት ቤትና ቅዱስ ገብርኤል ካቶሊክ ሚሽን እስከ 6ኛ ክፍል እንዲሁም በቀድሞ ከምባታ ሀዲያ አውራጃ ዋስገበታ ቅዱስ መስቀል መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተሰኘ ካቶሊክ ሚሽን ከ7ኛ እና 8ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በ1963 ዓ.ም አጠናቀዋል።
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በልጅ አበበ ወልደ ሰማዕት ወይም በአሁኑ ዋቸሞ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል በመከታተል በ1966ዓ.ም ያጠናቀቁ መሆናቸውን ከቤተሰቦቻቸውና ከቅርብ ጓደኞቻቸው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
በወቅቱ መንግስት 10ኛ ክፍልን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን መልምሎ ወደተለያዩ ኮሌጆች ይልክ ስለነበር ይህን እድል በመጠቀም ወደ ጎንደር ጤና ጥበቃ ኮሌጅ የገቡት አቶ ለገሰ በወቅቱ በነበረው “እድገት በህብረት”በተሰኘ ብሔራዊ ዘመቻ ሆሳዕና የስልጠና ጣቢያ በመቀላቀል በኋላም ወደ ዝዋይ፣ሮጲ፣አጄና ሀላባ በመዘዋወር የሁለት ዓመታት ግዳጃቸውን በታማኝነት ፈጽመዋል።
በ1969 ዓ.ም ግዳጃቸውን ፈጽመው ወደ ጎንደር ጤና ጥበቃ ኮሌጅ የተመለሱ ቢሆንም በወቅቱ በኢህአፓ፣መኤሶንና በደርግ መካከል በነበረው የፖለቲካ ትግል ምክንያት ስልጠናውን አቋርጠው በ1970 ዓ.ም በድጎማ መምህርነት ተቀጥረው በተወለዱበት አካባቢ በመምህርነት ህዝቡን ማገልገላቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል።
በኋላም እያስተማሩ የ12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በዱራሜ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምረው በማጠናቀቅ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን በመቀላቀል በአቢይና ንዑስ ትምህርት በሚባሉ ፖለቲካል ሰይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት እንዲሁም በህዝብ አስተዳደር የመጀመሪያ ድግሪያቸውን በ1980 ዓ.ም ካጠናቀቁ በኋላ በሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር በደህንነት ክፍል ባለሙያ በመሆንም አገልግለዋል።
ከ1985 ዓ.ም ጀምሮ በወቅቱ በነበረው መዋቅር የጠምባሮ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም ከ1987-1992 በወቅቱ ከምባታ ሀላባ ጠምባሮ ዞን ትምህርት መምሪያ በመዛወር አገልግለዋል።
በ1992 ዓ.ም በነበረው ብሔራዊ ምርጫ የ”ኢትዮጵያ አማራጭ ኃይሎች ህብረት”የተሰኘ የፖለቲካ ፓርቲን በመወከል ከ1993 እስከ 1997 በኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጠምባሮ ብሔረሰብ ተወካይ ነበሩ ።
በዚያን ወቅት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በክፍለ አህጉራዊና የአካባቢ ልማት ጥናት ትምህርት ተምረው ያጠናቀቁ ሲሆን ከ1998 እስከ 2000 ዓ.ም በቀድሞ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ የማህበራዊ ልማትና ሱፐርቪዥን ቡድን መሪ እንዲሁም ከ2000 ዓ.ም እስከ ጡረታ እስከወጡበት 2013 ዓ.ም ድረስ በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ በህግና ጎቨርናንስ ኮሌጅ በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግለዋል።
አቶ ለገሰ ሐንቆሬ ባለትዳርና የ2 ወንድና የ7ሴት ልጆች በድምሩ የ9 ልጆች አባት የነበሩ ሲሆን ባደረባቸው ህመም በህክምና ሲረዱ ቆይተው ሐምሌ 29 /2016 ዓ.ም በተወለዱ 69 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ጣቢያችን ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መጽናናትን ይመኛል።
ዘጋቢ -አማኑኤል አጤቦ ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ