38ሺ 855 ኮደሮችን በሶስት ዓመት ውስጥ ለማሰልጠን እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) 38ሺ 855 ኮደሮችን በሶስት ዓመት ውስጥ አሰልጥኖ ግቡን ለማሳካት እየሰራ መሆኑን የጌዴኦ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ አስታውቋል፡፡
ሁሉም ወጣቶች ተመዝግበው በኦንላይን በመሠልጠን አለም አቀፍ ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክህሎት ባለቤት መሆን እንደሚገባቸው ተገልጿል።
የጌዴኦ ዞን ሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምሪያ ኃላፊ አቶ ደረጀ ሾንጣ በሰጡት ማብራሪያ የኢትዮጵያ መንግሥት ከተባበሩት አረብ ኤሜሪትስ (UAE) ጋር በመተባበር 5 ሚሊዮን ወጣቶችን በኮደር ዲጂታል ኢኮኖሚ ለማሰልጠን ያለመ ፕሮግራም ማስጀመራቸውን አስረድተዋል።
መርሐግብሩ ለ3 ተከታታይ ዓመታት የሚቆይ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው ሥራ ያላቸውም ሆነ ሥራ የሌላቸው ወጣቶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ በመመዝገብ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚጠበቅባቸው አሳስበዋል።
በሀገር አቀፍ ደረጃ በነጻ ኦንላይን ለማሠልጠን በተያዘው ዕቅድ መሠረት በጌዴኦ ዞን 38 ሺህ 8 መቶ 55 ኮደሮችን በሶስት ዓመት ውስጥ አሰልጥኖ ግቡን ለማሳካት ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አቶ ደረጀ አክለዋል።
Programming Fundamentals፣ Data Science Fundamentals እና Android Developer Fundamentals በፕሮግራሙ የተካተቱ ስልጠናዎች መሆናቸውን ጠቁመው ስማርት ስልክ ያላቸውና ኮምፒውተር መጠቀም የሚችሉት በየትኛውም ደረጃ የሚገኙ ወጣቶች የሥልጠናው ተሳታፊዎች መሆን እንደሚችሉ አስታውቀዋል።
ስልጠናዎቹ “Udacity” በተሰኘው አለም አቀፍ እውቅና ባለው ኦላይን የትምህርት ፕላትፎርም ተዘጋጅቶ ይቀርባል ያሉ ሲሆን ወጣቶች የፈለጉትን ኮርስ ወይም መስክ መርጠው በኦንላይን መሠልጠን ይችላሉም ተብሏል።
ሰልጣኞች ያለምንም ክፍያ በነጻ ኮምፒውተራቸውን ወይም ስማርት ስልካቸውን ብቻ በመጠቀም ሀገሪቱ ከማኑዋል አሠራር ወደ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕድገት በምታደርገው ግስጋሴ የበኩላቸውን አሻራ ማሳረፍ ይጠበቅባቸዋል ብለዋልም።
የኦንላይን ስልጠናው ከ6-7 ሳምንታት ጊዜ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን በማመር ሐግብሩ ማጠቃለያ ላይ ዩዳሲቲ በተሰኘው ድርጅት አለም አቀፍ ሞያዊ ሰርተፊኬት ይሰጣል ሲሉ ተናግረዋል።
መምሪያው ከክልል፣ ከዞን፣ ከወረዳ፣ ከከተማ አስተዳደር ኃላፊዎችና ከንቲባዎች ጋር እንዲሁም ከሳይንስና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ጽሕፈት ቤቶች አመራሮች ጋር በዘርፉ ሰፊ ውይይት በማድረግ ወደሥራ መግባቱን ያወሱት አቶ ደረጄ፥ በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ዜጎችን ለማፍራት በሚደረገው እንቅስቃሴ ሁሉም የበኩሉን ሚና መወጣት ይኖርበታል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡ እስራኤል ብርሃኑ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ