የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

የአገልግሎት አሰጣጥን በማዘመን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ ተገለፀ

ሀዋሳ፡ ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በከተሞች የሚሰጡ አገልግሎቶችን በማዘመን ለነዋሪዎች ምቹ ማድረግ እንደሚገባ የሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ አስታውቋል።

የሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ “የዘመነ አገልግሎት ለከተሞች ብልጽግና “በሚል መሪ ቃል የ2017 በጀት ዓመት ዓመታዊ ጉባኤውን አካሂዷል።

የሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ አናም በዚህ ወቅት እንደገለጹት፥ በከተሞች በኮንስትራክሽን ሥራ ዘርፍ የሚታዩ መጓተቶችን ለማስቀረት በርካታ ተግባራት ማከናወናቸውን ገልፀው፥ አሁንም መስተካከል ያለባቸው ቀሪ ሥራዎች እንዳሉ አመላክተዋል።

የመሬት መብት መረጃ ምዝገባ ሥራ ለከተሞች ዕድገት ወሳኝ መሆኑን በመገንዘብ በዘርፉ ብቃት ያላቸው አመራሮችና ባለሙያዎች ባለመመደባቸው የከተሞችን ገቢ በአግባቡ መሰብሰብ አለመቻሉንም ጠቅሰዋል።

የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራትና የምዝገባ ሥራ በከተሞች በልዩ ትኩረት መሠራት እንደሚጠበቅም ኃላፊው አመላክተዋል።

ከህግ ተጠያቂነት ይልቅ የአገልግሎት አሰጣጥን ማዘመን ተገቢ በመሆኑ በተመረጡ የአገልግሎት ዘርፎች በተለይም በመሬት ልማት ማኔጅመንት፣ በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥና በዕለት ገቢ አሰባሰብ ሥራዎች ከእጅ ንክኪ ነፃ አገልግሎት መስጠት እንድችሉም አቶ ተሾመ ጥሪ አቅርበዋል።

በጉባኤው የ2016 በጀት ዓመት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቦ በተሳታፊዎች ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ ለከተሞች ዕድገት ማነቆ ናቸው ተብለው በተለዩ በውሃና መንገድ መሠረተ ልማት ጉድለቶችና በኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ ችግሮች ዙሪያ መሟላትና መሠራት የሚገባቸውን ጉዳዮች በማስመልከት ጥያቄዎች ቀረበዋል።

በመደረኩ የተገኙት የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ ከተሞች በዕቅድ መሠረት መልማትና ዘመናዊ እንድሆኑ በማድረግ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት መሠራት እንዳለበት ተናግረዋል።

በመሬት አስተዳደር ሥርዓት፣ በገቢ፣ በንግድ ሥራና የከተማ ልማት አፈፃፀም የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራሮችን ሁሉም አካላት በጋራ መታገል እንደሚገባም ዋና አስተዳዳሪ አስገንዝበዋል።

በአቋራጭ ለመበልፀግና ያልተገባ ጥቅም ለማግኘት በብልሹ አሠራሮች መሳተፍ በህግ እንደሚያስጠይቅ በመረዳት ከታሪክ ተወቃሽነትና ከህሊና ዝቅጠት ለመዳን አመራሮቹ የተጣለባቸውን አደራ በታማኝነት መወጣት እንደሚጠበቅባቸው አቶ ማቴዎስ አጽንዖት ሰጥተዋል።

በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ የከተማ አስተዳደሮች የዋንጫና የዕውቀትና የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።

ዘጋቢ፡ ኤልያስ ኤርሶ- ከሆሳዕና ጣቢያችን