የአፈር አሲዳማነትን በማከም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ኢንስቲትዩቱ አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ነሐሴ 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የአፈር አሲዳማነትን በማከም የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በሰሜን ቤንችና በጨና ወረዳዎች ላይ የሚሰራ የአሲዳማ አፈር ማሻሻያ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በጨና ወረዳ እያካሄደ ነዉ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሀብት ዘርፍ ተወካይና የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ አሚኖ መሐመድ፥ የአፈር አሲዳማነት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ይህንን በማከም ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንዲቻል እንደሀገር ለክልሉ 89 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በመስጠት 1 መቶ 5 ሺህ ኩንታል የግብርና ኖራ ተገዝቶ እንዲመጣ ተደርጓል ብለዋል።
እጅግ አሳሳቢ እየሆነ ያለዉን የአፈር አሲዳማነት በማከም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ትዉልድን ማስቀጠል እንዲቻል በምርምር የታገዘ የአፈር ማከም ስራን መደገፍ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በክልሉ ከመንግሥት በተጨማሪ የተለያዩ መንግታዊ ያልሆኑ ተቋማት በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራትን በማገዝ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ መሆኑንም አንስተዋል።
በመድረኩ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ተወካይ እና የስርዓተ ምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር ዶ/ር አብይ ገ/ሚካኤል፥ የአፈር አሲዳማነት በክልሉ ከፍተኛ ተፅዕኖ በማድረስ የምርት መጠን እንዲቀንስ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢንሰቲትዩቱ ይህንኑ ችግር ለመቅረፍ በክልሉ ከቤንች ሸኮ እና ከካፋ ዞን 3 ወረዳዎች ላይ የአፈር አሲዳማነት ለማከም የሚያስችል የምርምር ስራዎችን አርሶአደሮችን በማሳተፍ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የተጀመረው የጥናት ስራ በሁሉም ዘርፍ ዉጤታማ ሆኖ አርሶአደሮችን ተጠቃሚ ማድረግ እንዲችል የተቀናጀ ስራ ይጠበቃል ብለዋል።
የቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አስራት አለማየሁ በበኩላቸው፥ በክልሉ የግብርና ማነቆ የሆነውን የአፈር አሲዳማነት ችግር ለመፍታት በተደረገው ጥረት የተሻለ ዉጤት መመዝገቡን ገልጸዋል።
የአሁኑ መድረክም የአሲዳማ አፈር ችግሮችን ለመፍታት ከሰሜን ቤንችና ከጨና ወረዳ ከተውጣጡ አርሶደአሮችና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ ግንዛቤ መያዝ እንዲቻል የተዘጋጀ ነዉ ብለዋል።
በፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጨና ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተረፈ ገ/ማሪያም ክልሉ ከተመሰረተ ወዲህ የግብርና ምርታማነትን በሚያሳድጉ ስራዎች ላይ በሰጠዉ ትኩረት የተሻለ ዉጤት እየተመዘገበ ይገኛል ብለዋል።
በተለይም በየወቅቱ ለአርሶ አደሩ የሚሰጡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናዎች በዘርፉ በቂ እዉቀቶችን በመያዝ ማነቆዎችን መፍታት እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።
አርሶአደሮችም በስልጠናው የሚያገኙትን እዉቀት በአግባቡ መሬት ላይ በማውረድ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ አሳስበዋል።
ከክልሉ ግብርና ቢሮ ጋር በመተባበር በቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል በሰሜን ቤንችና ጨና ወረዳዎች ላይ የሚሰራ የአሲዳማ አፈር ማሻሻያ ሰርቶ ማሳያ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ በተለያዩ ተመራማሪዎች በአፈር አሲዳማነት ላይ የተዘጋጁ የምርምር ዉጤቶች ቀርበዉ ዉይይት እየተደረገበት ነዉ።
ዘጋቢ፡ አሰግድ ሣህሌ – ከቦንጋ ጣቢያችን

More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ