ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ሠሞኑን መንግስት በሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ዙሪያ የወሰዳቸው እርምጃዎችን ተከትሎ የሚመጡ ኢኮኖሚያዊ ተፅእኖዎችን መቋቋም የሚችል አቅም መፍጠር እንደሚያስፈልግ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡
ቢሮው በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ ትግበራ ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር የመግባቢያ መድረክ አካሂዷል።
ከአምስት አመታት አስቀድሞ ጥናት ሲደረግ የነበረው የሀገሪቱ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፖሊሲ መተግበሩን ተከትሎ እየተሰጠው ያለው ትክክል ያልሆነ ትርጉም በመሠረታዊ ሸቀጦች ላይ የዋጋ ንረት አስከትሏል።
ይህንን ተከትሎ በመሠረታዊ የሸቀጦች ዋጋ ላይ ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ ከዛሬ ጀምሮ ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚጀምር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ገሌቦ ጎልቶሞ የማክሮ ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን በአለም ደረጃ ተወዳዳሪ የኢኮኖሚ ባለቤት የሚያደርጋት ሆኖ ሳለ የንግድ ስርዓቱን በሚያዛባ መልኩ መተርጎም አግባብ አይደለም ብለዋል።
በክልሉ ከተሞች ከግብርና ምርቶች ጀምሮ የሸቀጦች ዋጋ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ለውጥ መታየቱን የተናገሩት አቶ ገሌቦ ይህ የዋጋ ጭማሪ ወደነበረበት እንዲመለስ ከዛሬ ጀምሮ ጠንካራ እርምጃ እንደሚወሰድም አፅንኦት ሠጥተዋል።
ይህን ያልተገባና ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪ ወደነበረበት ለመመለስ ማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ በማይችሉ የዞን መዋቅሮች ላይ አስፈላጊው የእርምት እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል የቢሮ ኃላፊው።
የዶላር ዋጋ መጨመሩን ተከትሎ በክልሉ በኢኮኖሚ አሻጥሩ ላይ እጃቸው ያለባቸውን ነጋዴዎችን ለማስተማር የተወሰደው የእርምት እርምጃ እዚህ ግባ የሚባል አለመሆኑን የተናገሩት ደግሞ የቢሮው ምክትል ኃላፊና የንግድ አሰራር ሬጉላቶሪ ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ፍቅርተ አበራ ናቸው።
በክልሉ ምርትን ከመደበቅ እስከማሸሽ የሚደርሱት ጥቂት የንግዱ ማህበረሰብ በአቋራጭ ለመክበር የሚያደርጉት ጥረት ነው ያሉት ወ/ሮ ፍቅርተ የክልሉ መንግስት ይህንን እኩይ ተግባር አይታገስም ብለዋል።
በምክክር መድረኩ ላይ ከተገኙት ዞኖች መካከል የጋሞና የኮንሶ ዞኖች የንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊዎች ወ/ሮ ደሳለች ዳዊት እና አቶ ዮሀንስ ኩስያ በበኩላቸው በየዞናቸው በሸቀጦች ላይ ከ2 መቶ እስከ 2 ሺህ ብር ድርስ ምክንያታዊ ያልሆኑ የዋጋ ጭማሪዎች መስተዋላቸውን ተናግረዋል።
በጋሞ ዞን ህገ-ወጥ ጭማሪ ባሳዩት 71 ነጋዴዎች ላይ ከማሸግ እስከ እስር የሚደርስ እርምጃ፤ በኮንሶ ዞን ደግሞ ከ16 በላይ ህገ-ወጥ ነጋዴዎች ላይ የማሸግ እርምጃ መወሰዱን የመምሪያ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ