የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት በዘርፉ የተሰማሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ተጠቆመ፡፡

የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት በዘርፉ የተሰማሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው ተጠቆመ፡፡

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 29/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመቅረፍ በሚደረገው ጥረት በዘርፉ የተሰማሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከፍተኛ አበርክቶ እንዳላቸው የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት አስታወቀ።

በአነስተኛ ቅድመ ክፍያና ወርሃዊ ቁጠባ የዜጎችን የመኖርያ ቤት ችግር ለመቅረፍ የተቋቋመው “ኪይ ሀውሲንግ ፋይናንስ ሶልሺን” (key housing finance solution)የተሰኘው ሀገር በቀል ተቋም በሆሳዕና ከተማ የማስተዋወቂያ ፕሮግራም አካሄዷል።

የኪይ ሀውሲንግ ፋይናንስ ሶልሺን መስራች አቶ ግሩም ይልማ  ተቋሙ ዜጎች ቤት መግዛት ”ቀላል ነው ”የሚል መርህ አንግበው በአነስተኛ ቅድመ-ክፍያ እና ወርሃዊ ቁጠባ በሚቀጥሉት አስር ዓመታት ውስጥ 1መቶ ሺህ ዜጎችን የመኖሪያ ቤት ባለንብረት ለማድረግና  ቤቶችንም በከፍተኛ ጥራት ገንብቶ ለማስተላለፍ አቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል ።

ተቋሙም ብዙዎችን ተጠቃሚ በማድረግ አነስተኛና መካከለኛ ገቢ ያለቸው ዜጎችና መንግሥት ሰራተኞች  በመረጡት የሀገሪቱ ከተሞች ዋስትና ተጠብቆላቸው፣ ያለ ጫና በረጅም ዓመታት ክፍያና ያለ ወለድ የቤት ችግርን መቅረፍ ዓላማው ያደረገ ስለመሆኑ አብራርተዋል።

በተቋሙ  የሆሳዕና ቅርንጫፍ አስተባባሪ ወይዘሪት ቤተልሔም በርተሎሜዎስ በከተማዋ ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት እጥረትና  ፍላጎት መኖሩ በጥናት ተለይቶ  ይህንን ችግር ለመቅረፍ ደንበኞች በሚቀጥሉት 30 ዓመታት በተዘጋጀው የአከፋፈል ስርዓት በርካቶችን የቤት ባለቤት ለማድረግ  ተቋሙ ወደ ስራ መግባቱን አስረድታለች ።

በማስተዋወቂያ ፕሮግራም የተገኙት የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ምክትል ስራ አስኪያጅና የቤቶች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ወንድሙ  የመኖሪያ ቤት ለሰው ልጆች ከሚያስፈልጉ መሠረታዊ ፍላጎቶች ዋንኛው መሆኑን በመጥቀስ ይህም በመንግሥት ብቻ የሚቀርፍ ባለመሆኑ ህጋዊ አሰራርን ተከትለው  የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሚወጡት አበርክቶ የላቀ መሆኑን ገልፀዋል ።

አቶ ዳንኤል አክለውም ተቋሙም የተለያዩ  ህጋዊ ማዕቀፎችን በመከተል በአነስተኛ ቅድመ ክፍያና ወርሃዊ ቁጣባ በርካቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ ፕሮግራሙን እንደሚደግፉና ለዚህም ከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ትብብር ያደርጋል ብለዋል።

ዘጋቢ፦ ሄኖስ ካሳ ከሆሳዕና ጣቢያችን።