ተመራቂዎች ለሀገሪቱ ብርሃን በመሆን ከሀሰተኛና ከጥላቻ ንግግሮች በመራቅ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ መደገፍ ይገባቸዋል – ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 28/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ተመራቂዎች ለሀገሪቱ ብርሃን በመሆን ከሀሰተኛና ከጥላቻ ንግግሮች በመራቅ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ መደገፍ እንደሚገባቸው የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት፣ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ አሳሳቡ፡፡
ዜድ ቫሊዩ ኮሌጅ የሆሳዕና ካምፓስ ለ2ተኛ ዙር በዲፕሎማ፣ በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ 6 መቶ 21 ተማሪዎችን አስመርቋል።
በምረቃ ስነ-ሰርዓቱ ላይ የዜድ ቫሊዩ ኮሌጅ ፕሬዚዳንት አቶ ዘውዴ ተሾመ እንዳሉት ኮሌጁ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለ2ተኛ ዙር በሁለተኛና በመጀመሪያ ዲግሪ እንዲሁም በዲፕሎማ መርሐግብር 6 መቶ 21 ተማሪዎችን ማስመረቅ ችሏል።
ተማሪዎች ከኮሌጁ በቀሰሙት እውቀትና ክህሎት በስራ ዓለም ተወዳዳሪ ከመሆንም ባለፈ በሕይወት ዘመናቸው ውጤታማ የሚሆኑ ተግባራት በቆይታቸው መከናወኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋን ለማፍራት ጥራት ያለው ትምህርት ወሳኝ በመሆኑ በተለያዩ ትምህርት ዘርፎች ለትምህርት ጥራት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ዘውዴ ተሾመ ተናግረዋል።
የቀለም ትምህርትን ከተግባር ትምህርት ጋር በማቀናጀት ተማሪዎች ብቃታቸውንና ክህሎታቸውን ማዳበር እንዲችሉ በትኩረት እየተሰረ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ተመራቂዎች መንግስትን ከመጠበቅ ስራ ፈጣሪ ዜጎች በመሆን ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉም አሳስበዋል።
የሀድያ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ ዶ/ር በፍቃዱ ገ/ሃና በበኩላቸው የትምህርት ተቋማት ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታና ለልማት ተጠቃሚነትና ተደራሽነት የድርሻቸውን የሚወጡ ዜጎችን ለማፍራት በጥናትና ምርምር የተደገፈ ስራዎችን በትኩረት መስረት አለባቸው ብለዋል።
የኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሰው ሀብት ልማት ስምሪትና የቴክኖሎጂ ሽግግር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢና የዕለቱ የክብር እንግዳ ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ፤ የተሻለ ሀገር ለመገንባት በሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም በጥናትና ምርምር ዘርፎች በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ትውልድን በስነ-ምግባርና በእውቀት መገንባት ለሀገሪቱ ሁለንታናዊ ለውጥ ወሳኝ እንደሆነም ዶክተር ነገሬ ገልጸዋል።
በሀገሪቱ የትምህርት ተደራሽነትንና ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ የመንግስትና የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመክፈት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዉ፤ የትምህርት ጥራትና የትምህርት ስርዓቱን ለማጠናከር የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም አመላክተዋል።
ተማሪዎች ለሀገሪቱ ብርሃን በመሆን ከሀሰተኛና ከጥላቻ ንግግሮች በመራቅ የተጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞው መደገፍ እንደሚገባቸውም ዶክተር ነገሬ ሌንጮ አስገንዝበዋል።
ተመራቂ ተማሪዎች በሰጡት አስተያየት በሰለጠኑበት የሙያ መስክ ስራ ጠባቂዎች ብቻ ሳይሆኑ ስራ ፈጣሪ በመሆን የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ: ተመስገን ታደለ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ