በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘመናዊና ተደራሽ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በተደረጉ ጥረቶች ውጤት ተመዝግቧል – የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 21/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘመናዊና ተደራሽ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት ለመገንባት በተደረጉ ጥረቶች ውጤት መመዝገቡን የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ ተናገሩ፡፡
የሀገሪቱን የንግድ ሥርዓት የሚጎዳው ህገ-ወጥ የኮንትሮባን እንቅስቃሴን ለመግታት የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑም ተመላክቷል፡፡
የገቢዎች ሚኒስቴር የ2016 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈፃፀሙን በአርባ ምንጭ ከተማ ገምግሟል፡፡
በግምገማ መድረኩ ላይ የተገኙት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ዘመናዊና ተደራሽ የታክስ ሥርዓት በመገንባት ሂደት ውስጥ አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል፡፡
ይህን ተከትሎ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ5 መቶ 12 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን የተናገሩት ሚኒስትሯ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ70.8 ቢሊዮን ብር ብልጫ እንዳለውም በንግግራቸው ወቅት አመላክተዋል፡፡
የሀገሪቱን የገቢ አቅም ለማጎልበት የታክስና ጉምሩክ አስተዳደር ሥርዓቱን ማዘመን እንደሚጠበቅ ያስታወሱት የገቢዎች ሚኒስትሯ ተከታታይነት ያለው የህግና የአሰራር ማሻሻያ ማድረግ ቁልፍ ጉዳይ ስለመሆኑም አፅእኖት ሰጥተዋል፡፡
ይህን ለውጥ አስጠብቆ ለማስቀጠል የታክስና ጉምሩክ የህግ ተገዥነት ላይ ማህበረሰቡን ማስተማርና ተገቢውን እርምጃ የመውሰድ ተግባራት ስለመከናወናቸውም አንስተዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት የታክስና የንግድ ማጭበርበርን በመከላከል ፍትሀዊ ቀረጥና ታክስ አከፋፈል ሥርዓትን ለማስፈን ጥረት ተደርጓልም ብለዋል፡፡
የእቃዎች ማከማቻና ማስተላለፊያ አካባቢዎችን በጥናት በመለየት ህገ-ወጥ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴዎችን በመግታት በርካታ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል ስለመቻሉም ወ/ሮ ዓይናለም ንጉሴ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ ላይ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎችን ጨምሮ ባለድርሻ አካላት ተገኝተው ምክክር አድርገዋል፡፡
ዘጋቢ፡ በኃይሉ ሙሉጌታ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ