በአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በዘንድሮ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ፋይዳ ያላቸው ችግኞች እንደሚተከሉ የጌዴኦ ዞን ደንና አከባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ገለጸ፡፡

በዞኑ የግብርና መምሪያና የደንና አከባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት አዘጋጅነት የ2016 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ ተከላ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በኮቾሬ ወረዳ ረኮ ተራራ ላይ ተካሂዷል፡፡

በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በተከሰተው የመሬት ናዳ ህይወታቸውን ላጡ ወገኖች የሂሊና ፀሎት በማድረግ በተጀመረው መረሀ ግብሩ የዞኑ አስተዳዳሪ ዶ/ር ዝናቡ ወልዴ የዞኑ መንግስት በወንድም የጎፋ ህዝብ በደረሰው የተፈጥሯዊ አደጋ ከልብ ማዘኑን ገልጸው አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

አክለውም እንደ ሀገር በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መረሀ ግብር ለመትከል ከታቀደው 7 ቢሊዮን ችግኝ ውስጥ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን በዞን ደረጃ ለመትከል መታቀዱን ገልጸው ከነዚህ ውስጥ 4 ነጥብ 8 ሚሊዮን የሚሆኑ ችግኞችን በነቃ የህዝብ ተሳትፎ በመታገዝ በአንድ ጀንበር ለመትከል ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የዞኑ ደንና አከባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ታደሰ በዕለቱ 26 ነጥብ 1 ሄክታር ስፋትና 2ሺህ 426 ሜትር ስፋት ባለውን የረኮ ተራራ ከአምስት ሺህ በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ፋይዳ ያሏቸውን ሀገር በቀልና የውጪ ዝሪያ ያላቸው ችግኞች መተከላቸውን ገልጸው በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ተራራውን ለማልማት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዞኑ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት አካል የሆነው ከ43 ሚሊዮን በላይ የእንሰትና ከ13 ሚሊዮን በላይ የቡና ችግኞች መተከላቸውን ያስረዱት አቶ ዮሐንስ፥ የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ ለአየር ንብረት የማይበገር አረንጓዴ አከባቢ ለመፍጠር የሚደረገውን ርብርብ ማገዝ የሁሉም ኃላፊነት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ያነጋገርናቸው የአረንጓዴ አሻራ ተከላ መረሀ ግብር ተሳታፊዎችም የቀደምት አባቶችን አደራ ተረክበው አረንጓዴ አከባቢን ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር በቁርጠኝነት እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን