የከተማውን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የከተማውን ሠላምና ፀጥታ ለማስጠበቅ ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት እየሠራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሀዲያ ዞን ፓሊስ መምሪያ አስታወቀ።
በሆሳዕና ከተማ በሚገኙ ስድስት ቀበሌ ማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ኮንፈረንስ ተካሂዷል።
የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ጽ/ቤት አዛዥ ም/ኮማንደር ጥጋቡ ቀጭኔ እንደገለጹት ከሀድያ ዞንና ከሌሞ ወረዳ የፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የከተማውን ሠላም ለማስጠበቅ በትጋት እየተሠራ ነው።
በከተማው የሚደረጉ የተለያዩ ክብረ በዓላት፣ መንግሥታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ መሰናዶዎች እንዲሁም ህዝባዊ እንቅስቃሴዎች በሰላም እንዲከናወኑ የፖሊስ ጥረት ከፍተኛ እንደነበረ ም/ኮማንደሩ አስተውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ የወንጀል መከላከል ግብረ ሀይል በመቋቋም የአከባቢውን ደህንነት የማስጠበቁ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉንም አመላክተዋል።
በከተማው የተደረገው ማህበረሰብ አቀፍ የወንጀል መከላከል ኮንፍረንስም ይህንን ተግባር ከግብ ለማድረስ የላቀ ሚና እንዳለው ም/ኮማንደር ጥጋቡ ተናግረዋል ።
በ238 የፖሊስ አባላት አማካኝነት የተለያዩ የወንጀል ድርጊት የሚፈጽሙ አካላትን በህግ እንዲጠየቁ እየተደረገ መሆኑን የጠቆሙት አዛዡ ማህበረሰቡ ማንኛውንም ዓይነት የወንጀል ድርጊት ሲፈጸም ለፖሊስ መረጃ በመስጠት እንዲተባበር ጠይቀዋል ።
የሆሳዕና ከተማ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መስተዳድር መቀመጫ እንደመሆኗ ሰላሟ የተጠበቀ እንዲሆን በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የሀድያ ዞን ፖሊስ አዛዥ ዋና ኢንስፔክተር ተሾመ ባቲሶ ናቸው ።
በሆሳዕና ከተማ የተጀመረውን ህዝባዊ ንቅናቄ በዞኑ በሚገኙ በሃያውም መዋቅር አጠናክረው እንደሚያስቀጥሉ ዋና ኢንስፔክተሩ ጠቁመዋል።
በየመንደሩ ህዝባዊ ሠራዊት በመገንባት የአከባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ እየተሠራ ነው ያሉት ዋና ኢንስፔክተር ተሾመ ማህበረሰቡም ከፀጥታ አካላት ጎን በመሆን በነቃ ስሜት ወንጀልን በጋራ መከላከል ያስፈልጋልም ብለዋል ።
የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎችም ፕሮግራሙ እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አንስተው ትውልድን በስነምግባር አንጾ ማሳደግ እና የወንጀልን ተግባር ከቤተሰብ ጀምሮ መከላከል እንደሚገባ ተናግረዋል።
በወንጀል ተይዘው ለህግ በሚቀርቡ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ ለወሰድ እንደሚገባ ነዋሪዎቹ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በዕለቱም ከሱስ፣ ከመዝናኛ ማዕከላት፣ ከትራፊክ ፍሰትና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዞ ወንጀል ከመከላከል ረገድ ከተሳታፊዎች ጋር ሰፊ ውይይት ተደርጓል።
ዘጋቢ፡ መንግሥቱ ፊጣሞ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ