ለትምህርት ስርዓት ውጤታነት ትኩረትን መስጠት የሁሉም ትምህርት ማህበረሰብ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ለትምህርት ስርዓት ውጤታነት ትኩረትን መስጠት የሁሉም ትምህርት ማህበረሰብ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል – ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለትምህርት ስርዓት ውጤታነት ትኩረትን መስጠት የሁሉም ትምህርት ማህበረሰብ ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር እንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ትምህርት ቢሮ አዘጋጅነት “የተማረ ዜጋ ለሁለንተናዊ ብልጽግና!” በሚል የተዘጋጀ የንቅናቄ መድረክ እየተካሄደ ይገኛል፡፡

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ዶ/ር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እንደገለጹት በትምህርት ሥራዎች ባለፉት ጊዜያት የታዩ የትምህርት ስርዓት ስብራቶች ተብለው የተለዩትን ጉዳዮች ምላሽ መሠጠት ይገባል።

ለትምህርት ስርዓት ውጤታማነት ትኩረት መስጠት የሁሉም ትምህርት ማህበረሰብ ኃላፊነት በመሆኑ ይህንን በመገንዘብ ወደ ተግባር መግባት ይገባል ብለዋል።

መምህራን ለትምህርት ስራ ውጤት ዋነኛ ተዋናይ በመሆናቸው በዚህም መምህራንን ለማብቃት፣ የመምህራን ጥያቄ ለመፍታት ሥራዎች የተሠሩበት ዓመት ነው፡፡ ነገር ግን በቂ ነው ተብሎ የማይታሰብ በመሆኑ ለመምህራን ኑሮ ማሻሻያ ተግባራት ለአብነትም በቁጠባ ቤት እንዲገነቡ በከተማ አስተዳደሮች በኩል መግባባት የተቻለበት እንደሆነ ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

በትምህርት ቤቶች የታዩ ውስንነቶችን ለመፍታት በቀጣይነት የሚሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

መምህራን ለትምህርት ስራ ውጤታማነት ያላቸው ድርሻ የጎላ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለትምህርት ስራዎች ውጤታማነት መምህራን ዝግጅት በማድረግ ተግባራዊ ሊያደርጉ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ትምህርት ቢሮ ኃላፊና የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪ አቶ አልማው ዘውዴ፤ በትምህርት ዘመኑ ማህበረሰብን ባሳተፈ መልኩ በተሠራው ሥራ 434 ሚሊዮን ብር ግምት ያለውን ሃብት በገንዘብ፣ በጉልበትና በአይነት ማንቀሳቀስ ተችሏል ብለዋል።

በክልሉ 896 አዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታ፣ ከ1282 በላይ ጥገና ማድረግ የተቻለበት ውጤት የትምህርት ለትውልድ ተግባራትን ማሳካት የተቻለበት ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የትምህርት ስኬት መሠረቱ በተቀረጸው የትምህርት ስርዓት ይገለጻል ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ይህንኑ ተልዕኮ ለመወጣት የጋራ ምክክር በማድረግ እጅግ የላቀ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።

በ2016 የትምህርት ዘመን የንቅናቄ መድረክ የመጽሐፍት ህትመትን ማድረግ የተቻለበት ነው። በዚሁም በህዝብ፣ በባለሃብቶችና በመንግሥት ርብርብ በማሳተም ለትምህርት ማህበረሰብ እንዲዳረስ ማድረግ የተቻለበት ዓመትም ነበር ሲሉ አስታውሰዋል።

ለ2017 የተጀማመሩ ተግባራትን በማጠናከር ማህበረሰብን የትምህርት ስኬትና ጉድለቶችን በመለየት ለተግባራዊነቱ ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ ማድረግ የሚገባ ነው ሲሉም አቶ አልማው ተናግረዋል።

የትምህርት ቤት ማሻሻያ ተግባራትን ባለፈው ዓመት መልካም ተሞክሮን በማስፋት በጊዜ የለኝም መንፈስ ለተግባር ርብርብ ማድረግ ይገባል ሲሉ አቶ አልማው ጠቁመዋል።

የ2017 ትምህርት ዘመን ክልላዊ የዝግጅት ምዕራፍ ሰነድ ቀርቦ ውይይት የሚደረግበት ስለመሆኑ ታውቋል።

ዘጋቢ፡ አዲስዓለም ታዬ – ከዋካ ጣቢያችን