የተራቆተ አከባቢን መልሶ ለማልማት ችግኝ መትከል አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

የተራቆተ አከባቢን መልሶ ለማልማት ችግኝ መትከል አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑ ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 17/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተራቆተ አከባቢን መልሶ ለማልማት ችግኝ መትከል ያለው አስተዋጽኦ የጎላ መሆኑን በዳውሮ ዞን የከጪ ወረዳ አስተዳዳር አስታወቀ፡፡

በወረዳው ሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም አማካይነት የተዘጋጀ የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተካሂዷል።

የዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር በዳውሮ ዞን ከጪ ወረዳ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት የከጪ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ውለታው ሁሴን ህብረተሰቡ ችግኝ ለመትከል ያለው ተነሳሽነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መጨመሩን ገልፀዋል ።

ወረዳው ከዚህ በፊት በተፈጥሮ ደን ሽፋን የሚታወቅ አከባቢ እንደሆነ የገለፁት ዋና አስተዳዳሪው አባቶቻችን ጠብቀው ያቆዩትን ደንን አሁን ያለው ትውልድ በአግባቡ ጠብቀው ለቀጣይ ትውልድ ማስተላለፍ ይጠበቃል ብለዋል።

አስተዳዳሪው አክሎም ችግኝ ተክሎ መተው ብቻ ሳይሆን የተተከሉ ችግኞች ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በመንከባከብ ሀላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል ።

የሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ተክለብርሃን ዘለቀ ፕሮግራሙ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዳውሮና ኮንታ ዞኖች ስድስት ወረዳዎችን በማቀፍ የበካይ ጋዝ ልቀት ቅነሳ ላይ ትኩረት በማድረግ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በዚህም የተፈጥሮ ደንን በመከለል፣ ችግኝ ጣቢያዎችን በማዘጋጀት፣ ችግኝ በማፍላትና ተከላ በማድረግ፣ የተራቆተ አከባቢዎች መልሰው እንዲለሙ ማድረግ ዋና ስራ እንደሆነ ጠቁመዋል ።

በስራው ወደ 47 ሺህ ሄክታር መሬት በደን መከለል መቻሉን እንዲሁ ።

የዳውሮ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊና ተፈጥሮ አከባቢና ደን ጥበቃ ዘርፍ ሀላፊ አቶ ምትኩ ላይኩን በዞኑ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በበልግና በመኸር ተከላ ጊዜ 43 ሚሊየን በላይ ችግኝ መተከል መቻሉን አስረድተዋል ።

በዚህም ሀገር በቀል፣ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸውና ለምግብነት የሚያገለግሉ ችግኞች ላይ ልዩ ትኩረት በማድረግ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዘንድሮው ዓመት እንደ ዞን 72 ሚሊየን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ም/ሀላፊው አሁን የተከላው ሂደት በጥሩ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ገልፀው ለዚህም ደግሞ የሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት ፕሮግራም ትልቁን ሚና እየተወጣ እንዳለ አብራርተዋል ።

የሬድ ፕላስ ኢንቨስትመንት የወረዳ ኮርዲኔተር አቶ ደመቀ ደሳለኝ ፕሮግራሙ በወረዳ ደረጃ 250 አባላትን በማህበር በማደራጀት ህብረተሰቡ በደን ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የመከላከልና ደን ተጠብቆ እንድቆይ የማድረግ ስራ በስፋት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል ።

በተከላ መርሃ ግብር አስተያየታቸውን የሰጡ ነዋሪዎቹ ችግኝ መትከል የሚያበረክተው አስተዋጽኦ የጎላ በመሆኑ የተተከሉ ችግኞች ለታለመለት አላማ እንዲውል በመንከባከብ ሀላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ አማኑኤል ተገኝ – ከዋካ ጣቢያችን