በአረንጓደ አሻራ የሚተከሉ ችግኞች ከምግብነት ባለፈ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እየተሠራ ነው
በመካሄድ ላይ ያለው የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር የአርብቶ አደሩን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የገቢ ምንጭ እንዲሆን እየተሰራ እንደሆነ በደቡብ ኦሞ ዞን የኛንጋቶም ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።
“የምትተክል ሀገር፤ የሚያፀና ትውልድ” በሚል መሪ ቃል በሀገር አቀፍ ደረጃ የተጀመረው የአረንጋዴ አሻራ መርሀ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን ኛንጋቶም ወረዳ ከ2 ሺህ በላይ የሙዝ ችግኝ ተተክሏል።
በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብረሃም ቦንገዞ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሐሳብ አመንጭነት የተጀመረው ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያላቸው ችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በኛንጋቶም ወረዳም ትኩረት ተሰጥቶት እየተሠራ ባለው ከዘርፉ አርብቶ አደሩ የራሱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባለፈ የገቢ ምንጭ እንዲሆንለት ጭምር ታስቦ እየተሠራ ይገኛል።
አስተዳዳሪው አክለውም ከተተከሉ የሙዝ ችግኞች አርብቶ አደሩን ይበልጥ ተጠቃሚ ለማድረግ ባለድርሻ አካላትና ወጣቶች አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አንዱ የብልጽግና ማረጋገጫ ራዕያችን ነው ያሉት የኛንጋቶም ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊና የወረዳው መንግሥት ዋና ተጠሪ ኢንጂነር ሳሙኤል ጃክሰን፤ ማህበረሰቡ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞችን በመከታተልና በመንከባከብ ወደፊት ከሚሰጠው ፍሬ የተሻለ ጥቅም ለማግኘት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
የኛንጋቶም ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታደለ በቀለ በበኩላቸው አርብቶ አደሩ ከዚህ ቀደም ከተተከሉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረው በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር 31 ሺህ 8 መቶ የደን፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ችግኞች መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ 2 ሺህ 2 መቶ የሙዝ ችግኞች መተከላቸውን ተናግረው አርብቶ አደሩ ከዚህ ቀደም በአረንጓዴ አሻራ ከተተከሉ የሙዝ፣ የማንጎ፣ የፓፓያና የአቮካዶ የፍራፍሬ ተክሎች ከራሳቸውና ከአካባቢው ማህበረሰብ ባለፈ ለአጎራባች አካባቢዎች በማቅረብ ገቢ ማግኘታቸውን ተናግረው በቀጣይ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚሰራ አስረድተዋል።
የወረዳው ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካረ አቦሎ፤ በአረንጓዴ አሻራ የተተከሉ ችግኞች በቂ ውሃ አግኝተው የተሻለ ምርት እንዲሰጡ ባለሙያዎች መመደባቸውን ተናግረው አርብቶ አደሮችና ሌሎችም ችግኞችን መትከል ብቻ ሳይሆን ፀድቀው አስፈላጊውን ምርት እንዲሰጡ እንክብካቤ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: በናወርቅ መንግስቱ – ከጂንካ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ