አቶ አሻግሬ ጀምበሬ
የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን አቶ አሻግሬ ጀምበሬ ይባላሉ፡፡ ትውልዳቸው በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አለታ ጩኮ ወረዳ ነው፡፡ የአንደኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአለታ ጩኮ ተምረዋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም የመጀመሪያ ድግሪ በኢዱኬሽናል ፕላኒንግና ማናጅመንት የ2ኛ ድግሪያቸውን ደግሞ በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን ተምረዋል፡፡ ከመምህርነት አስከ መንግስት የሥራ ኃላፊነት ለ 17 ዓመታት አገልግለዋል። አሁን ላይ የሲዳማ ክልል ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ከተሞችን በማዘመን ለነዋሪዎች ምቹ ከማድረግ አኳያና ተያያዥ ጉዳዮች አስመልክተን ከእሳቸው ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ፡፡
በደረጀ ጥላሁን
ንጋት፦ እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ በመሆንዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አሻግሬ፦ እኔም ለተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፦ በክልሉ ያሉ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ከማድረግ አኳያ የተከናወኑ ተግባራት ምን ይመስላሉ?
አቶ አሻግሬ፦ ቢሮው በዋናነት በክልሉ ያሉ ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ለማድረግ እንዲሁም በከተሞች ያለው የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ወቅቱ የሚፈልገውን እና በምህንድስናው ጥበብ ዘመን ተሻጋሪ ግንባታዎች እንዲከናወኑ በማድረግ ለከተማ ነዋሪዎች የተቀላጠፈ አገልግሎት የማቅረብ ዓላማ በማንገብ የተለያዩ ተግባራት አከናውኗል፡፡
በሲዳማ ክልል ሰባ አንድ ከተሞች አሉ። ሀዋሳ ከተማ ሪዮፖሊስቲ ሬጂዎ ፖሊስ /መሪ ከተማ/ ሲሆን በፈርጅ ሁለት 2፣ በፈርጅ ሶስት 4፣ ፈርጅ አራት 18 እና ቀሪዎቹ 46 ከተሞች ፈርጅ 5 ናቸው። ከተሞቹን በየደረጃው ከሚገኙ የሥራ ኃላፊዎችና ባለሞያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በጋራ በተሰራው ሥራ ሁሉም ከተሞች በፕላን እንዲመሩ ተደርጓል፡፡ ወደ ከተሜነት የሚያድጉ የገጠር ማእከላትን እያደጉ ሲሄዱ የኢኮኖሚ ጉዳት በማያደርስ መልኩ ከወዲሁ ስኬች ፕላን እየተዘጋጀ ነው፡፡
በክልሉ ያሉ ከተሞች የአመሰራረት ሥርዓታቸው እና እድሜያቸው የተለያየ ሲሆን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፉ ይሄዳሉ፡፡ ከተሞች እየሰፉ የሚሄዱት ደግሞ በገጠር ይዞታነት ወዳሉት ነው። ከዚህ አኳያ በከተሞች ፕላን የማስከበርና ድንበር የማዋሰን ሥራ ተሰርቷል፡፡ በሰሜናዊ ዞን ለኩ እና ወንዶ ገነት ከተማ አስተዳደሮች በፕላኑ መሠረት ወሰን የማስከበር ሥራ ተሰርቷል፡፡
በይርጋለም ከተማ ቀደም ሲል ከነበረው በተጨማሪ ከ 3 ሺህ ሄክታር በላይ በማካለል በስድስት የገጠር ቀበሌያት የሚኖሩ ከ30 ሺህ ህዝብ በላይ ወደ ከተማው ተካሏል፡፡ ምስራቃዊ ዞን ዳዬ ከተማ አስተዳደር 4 ሺህ ሄክታር ወደ ከተማ የተከለለ ሲሆን በስድስት ቀበሌያት የሚኖሩ ከ40 ሺህ ህዝብ በላይ ወደ ከተማ ተካቷል፡፡ በሌሎች ከተሞችም ፕላን የማሻሻልና መሠረታዊ ፕላን ተሰርቶላቸዋል፡፡
ንጋት፦ ለመኖር አስፈላጊና መሰረታዊ ከሚባሉት ውስጥ መጠለያ አንዱ ሲሆን በከተሞች ለዜጎች ቤት ለማቅረብ የተሰሩ ሥራዎች እንዴት ይገልፃሉ?
አቶ አሻግሬ፦ ሰዎች ወደ ከተማ በተለያዩ ምክንያቶች ለመኖር ይመጣሉ፡፡ ለዚህም ዜጎች የመኖሪያና የመስሪያ ቤት አግኝተው እንዲኖሩ ሁኔታዎች ሊመቻች ይገባል፡፡ ለዚህም መሬት እና ሌሎች አማራጭ የቤት መስሪያ መንገዶችን ማቅረብና ማመቻቸት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አኳያ በዚህ አመት 800 ሄክታር መሬት በክልሉ ላሉ ከተሞች ለማቅረብ ታቅዶ 88 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡ ይህም እንደየከተሞቹ ደረጃ መሬት በሊዝ ለኢንቨስትመንትና ለተለያዩ ንግድ ሥራዎች እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
መሬትን ለሁሉም በነፍስ ወከፍ ማድረስ ስለማይቻል አማራጭ የቤት አቅርቦት ላይ ተሰርቷል፡፡ በተወሰኑ ከተሞች ከ60 በላይ ማህበራት ተደራጅተው ግማሽ ቢሊዮን የሚሆን ገንዘብ የቆጠቡ ሲሆን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ቅድመ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡ ቀደም ሲል በማህበር መሬት የወሰዱና በተለያዩ ምክንያቶች ያልገነቡ 150 የሚሆኑ የተለያየ ደረጃ ያላቸው ቤቶች እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡
ሀዋሳ ላይ በመንግስት ወጪ ቆጣቢ በሆነ መንገድ የተገነቡ 328 ቤቶች ለዜጎች ለማስተላለፍ እንዲቻል የሚመሩበት የህግ አካሄድ ተጠናቋል። አለአግባብ ተጠቃሚ እንዳይኮንም ሶፍት ዌር ለምቶ ሥራ ላይ ለማዋል ሂደቱ ተጠናቋል፡፡ ከዚህ ሌላ በሀዋሳ ከተማ በሪል ስቴት የለሙ ቤቶች አሉ። በተጨማሪም ወጪ ቆጣቢ የሆኑ፣ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉ የህብረተሰብ ክፍሎች የተዘጋጁ 250 ቤቶች የማስተላለፍ ሥራ ተሰርቷል።
ግለሰቦች ባላቸው መሬት ላይ ራሳቸው ገንብተው በኪራይ ለዜጎች እንዲያቀርቡ የሚደረግበትም አካሄድ አለ፡፡
ከላይ ከተጠቀሱት አማራጮች መጠቀም ያልቻሉ እና ቤት ተከራይተው ለሚኖሩት ዜጎች መንግስት በቅርቡ አዋጅ አውጥቷል፡፡ የግል የኪራይ ቤቶች አስተዳደር አዋጁ ተግባራዊ እንዲሆን ሀዋሳ ላይ እየተሰራ ነው፡፡ አዋጁ አከራይና ተከራይ እኩል መብት እንዲኖራቸው ያደርጋል፡፡ አላስፈላጊ የቤት ኪራይ እንዳይጨምር፣ አከራይ በፈለገው ጊዜ ተከራይን ማስወጣት እንዳይችል ተከራይም የተከራየውን ቤት እንደራሱ አድርጎ በአግባቡ እንዲይዝ የሚያደርግ ነው፡፡ አዋጁ በአከራይና ተከራይ መካከል ሚዛን የማስጠበቅ ሥራ የሚሰራ ነው፡፡
ንጋት፦ የቤቶች አቅርቦት በበቂ ደረጃ ተሰርቷል ብለው ያምናሉ?
አቶ አሻግሬ፦ ቤቶችን በቂ በሚባል ደረጃ አቅርበናል የሚል ግምገማ የለንም፡፡ በክልሉ በተለያዩ ፕሮግራሞች ከሚሰሩ ስራዎች በተጨማሪ የኪራይ ቤቶች አስተዳደር ቁጥጥር አዋጅ የኪራይ ቤቶችን ለሚገነቡ ሰዎች በተለየ መልኩ ማበረታቻ አስቀምጧል፡፡ ይህም ቤት ገንቢዎችን የሚያነሳሳ ይሆናል፡፡ ሌላው አማራጭ ቤት ለሚገነቡ በክልሉ ካሉ ባንኮች ጋር አስተሳስረናል፡፡ ዜጎች የተወሰነ ሲቆጥቡ ባንኮች ለግንባታ እንዲያበድሩ የማድረግ ሥራ እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ሀዋሳ ላይ ሲዳማ ባንክ እየሰራ ይገኛል፡፡ የማህበር ቤት አንዲሁም ኮንደሚኒየም ቤት በመገንባት ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ እየተሰራ ነው፡፡ እነዚህ ሥራዎች ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ እገዛ አላቸው፡፡
ንጋት፦ በስፋት የሚስተዋለው ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት በቤት ፍላጎት ላይ የሚፈጠረውን ጫና ለማቅለል ምን ተሰርቷል?
አቶ አሻግሬ፡- ከተሞች በባህሪያቸው የስበት ማእከል ናቸው፡፡ ሰዎች ካሉበት አካባቢ በኢኮኖሚና ሌሎች ጉዳዮች ወደ ከተማ ይሰደዳሉ። ቀደም ሲል በክልሉ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በተጠናው ጥናት እንደተመለከተው በዋናነት በሁለት መንገድ ወደ ከተማ የሚደረግ ፍልሰት መኖሩን ያሣያል። የተለያዩ ሥራ ሰርተው ወደ አካባቢያቸው የሚመለሱ አንዱ ሲሆን ሌላው ደግሞ በቋሚነት ኑሯቸውን በጎዳና ያደረጉ ናቸው።
ችግሩን ለመፍታት የተሰሩ ሥራዎች መሰረታዊ ለውጥ አላመጡም፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከሀዋሳ ሀይቅ ማዶ ኤልሻዳይ የስልጠና ማእከል ተቋቁሞ አጫጭር ሥልጠናዎችን ከወሰዱ በኋላ ሥራ ማስጀመሪያ ገንዘብ በመስጠት እንዲሰሩ ቢደርግም ተመልሰው ወደ ከተማ ይመጣሉ፡፡ ሌላው ከጎዳና ላይ በማንሳት ወደ አካባቢያቸው እንዲመለሱ የተሰራው ስራ ውጤት አላመጣም። በአጠቃላይ በከተሞች የሚፈጠረውን ጫና በዘላቂነት ለመፍታት ራሱን የቻለ ቡድን ተመስርቶ ጥናት እየተደረገ ነው፡፡
አለምአቀፍ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከተሜነት እየሰፋ የሚሄደው በፍልሰትም ይሁን በአማራጭ ዜጎች ወደ ከተማ በመግባታቸው ነው፡፡ የተባበሩት መንግስታት ጥናት እንደሚያሳየው ደግሞ በ2050 በአለም አቀፍ ደረጃ 70 በመቶ ከተሜ ይሆናል። ወደ ሲዳማ ስናመጣው በየኪሎ ሜትሩ ከተሜነት የሚታይ በመሆኑ መቶ በመቶ ወደ ከተሜነት የመመለስ እድል አለው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሊገታ የሚችል ሥራ እየተሰራ ይገኛል፡፡
ንጋት፦ ከፕላን ውጪ የሚገነቡ ቤቶችና የመሬት ወረራን ለመከላከል ምን እየተሰራ ነው?
አቶ አሻግሬ፦ ዜጎች ቤትን በህጋዊ መንገድ ብቻ እንዲያገኙ ለማድረግ የተለያዩ አማራጮች ተዘርግተው እየተሰራበት ነው፡፡ በቂ ባይሆንም በተቻለ መጠን ህጋዊ በሆነ መንገድ በተሰጡት አማራጮች እንዲሳተፉ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከተሞች በፕላን ሲመሩ ዘመናዊና ለነዋሪዎቻቸው የተመቹ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ አኳያ ፕላንን የማስጠበቅና ህገ ወጥ የመሬት ወረራን የመከላከልና እርምጃ የመውሰድ ስራ እንሰራለን። በዚህም 240 የሚሆን በህገ ወጥ መልኩ የተገነቡ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ማፍረስ ተችሏል፡፡ እንዲሁም ከ320 ሄክታር በላይ መሬት የማስመለስ ሥራ በአመቱ ተሰርቷል፡፡
ንጋት፦ የፍትሀዊነት ጥያቄ የሚነሳባቸው የመንግስት ቤቶች ጉዳይን እንዴት ያዩታል?
አቶ አሻግሬ፦ የመንግስት ቤት ተብለው የሚጠቀሱት በአዋጅ የተወረሱ ቤቶች ናቸው። የሚተዳደሩበት የአመራር ሥርዓታቸው ራሱን የቻለና እንደክልሉ ነባራዊ ሁኔታ አዋጁን መሰረት ያደረገ መመሪያ አለ፡፡ ቤቶቹ ቅድሚያ ሊሰጥ የሚገባው በየትኛውም ደረጃ ላለና ቤት ለሌለው ሰው ነው፡፡ የሚነሱ የፍትሀዊነት ጥያቄዎችን በየደረጃው ለማረም ቤቶቹን የማስተዳደር ሥርዓት በመከተል የሚሰራ ነው፡፡ ያረጁና እድሳት የሚፈልጉትን እንዴት እናድሰው የሚለው አንዱ ሲሆን ሌላው የማሸጋገር ሥርዓቱ ነው፡፡ በዚህ መሰረት በዚህ አመት ሶፍት ዌር ለምቶ መረጃውን ዳታ ውስጥ እያስገባን ነው፡፡ ሀዋሳ 90 በመቶ ተጠናቋል፡፡ ይርጋለም ከተማ የተጠናቀቀ ሲሆን የሌሎች ከተሞችም በጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡
በዚህም የተለየው ጉዳይ አንዱ ቤቱን የያዘው ግለሰብ ተገቢ መሆኑን ማረጋገጥ ሲሆን ሌላው የቤቱ ይዞታ ቀድሞ የነበረውን መረጃ የማጥራት ጉዳይ ነው፡፡ ሂደቱም ችግሩን ለመለየት ይረዳል። ለምሳሌ ሀዋሳ ከተማ ላይ ከሰማኒያ ቤት በላይ ቤት ኖሯቸው ለመንግስት ከ200 እስከ 250 ብር እየከፈሉ እነሱ የራሳቸውን ቤት አከራይተው ከ40 እስከ 50 ሺህ ብር የሚወስዱ መኖራቸው ተለይቶ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ከከተማ አስተዳደር ጋር እየተሰራ ነው፡፡
ሌላው ከስራ ባህሪይ አኳያ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ያሉበት አካባቢ ለሥራ ምቹ የማይሆን ከሆነ የመንግስት ቤት ይሰጣቸዋል። ይህ በመመሪያ የተፈቀደ ነው፡፡ በአጠቃላይ በመንግስት ቤቶች ላይ የሚታየውን ኢፍትሀዊነት ለማረም ቴክኖሎጂን መሰረት ያደረገ አሰራር ተዘርግቶ እየተሰራበት ይገኛል፡፡
ንጋት፦ በከተሞች የመሠረተ ልማትን ከማስፋፋት አንፃር የተሰሩ ሥራዎችን ቢጠቅሱልን?
አቶ አሻግሬ፦ መሠረተ ልማት በክልሉ መንግስት በሚመደብ በጀት የሚሰራ ሲሆን በየደረጃው ያሉ የከተማና ወረዳ አስተዳደሮች በራሳቸው በጀት እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ ለመስራት ነው እቅድ የተያዘው፡፡ በዚህም በበጀት አመቱ በክልሉ መንግስት በ 24 ከተሞች 80 ኪሎ ሜትር የጠጠር መንገድ ተሰርቷል፡፡ 8 ኪሎ ሜትር የጎርፍ መውረጃ ቦይ በተለያዩ ከተሞች ተገንብቷል፡፡ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ በዳዬና ጎርቼ ከተሞች ተሰርቷል፡፡
ሌላውና ለከተሞች አስፈላጊ ከሆነው አንዱ የቄራ ግንባታ ነው፡፡ ያዬ ከተማ ዘመናዊ ቄራ እየተገነባ ሲሆን በሶስት ወር ተጠናቆ ሥራ ይጀምራል፡፡ ሀዋሳ ላይ የተሰራው የፍየልና በግ ቄራ በሀገር ደረጃ ከአራት ከተሞች ግምባር ቀደም ነው፡፡ ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ ከተሞች ራሳቸው የከተሞቻቸውን ገጽታ በመቀየር ለዜጎቻቸው ምቹ የማድረግ ሥራ ይሰራሉ፡፡ በራሳቸው በጀት 26 ኪሎ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ እንዲሁም 32 ኪሎ ሜትር ውሀ መውረጃ ቦይ እና የጠጠር መንገድም ሰርተዋል፡፡ በተመሳሳይ ፕላንን የማስጠበቅና አዳዲስ መንገድ ለመስራት በታቀደው መሰረት በ71 ከተሞች ላይ 124 ኪሎ ሜትር መንገድ የመክፈት ሥራ ተሰርቷል፡፡
ከተሞች ለነዋሪዎቻቸው ምቹና ሳቢ ሆነው ኢኮኖሚን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ ለማድረግ የአረንጓዴ ልማት ሥራ በትኩረት እየተሰራ ነው። ፕላን ሲዘጋጅ 30 በመቶ ለአረንጓዴ ልማት፣ 30 በመቶ ለመንገድና መሰረተ ልማት ዝርጋታ እና 40 በመቶ ደግሞ ለተለያዩ ግንባታዎች የሚውል ነው። ይህን በማስጠበቅ እየተሰራ ሲሆን አጠቃላይ በክልሉ ባሉ ከተሞች የአረንጓዴ ሽፋን 23 ነጥብ 5 በመቶ አካባቢ ደርሷል፡፡ ይህም እየጨመረ የሚሄድ ነው፡፡
ከተሞች ጽዱ እንዲሆኑ በፕላን በተዘጋጀው መልኩ የቆሻሻ መጣያ ቦታዎች እንዲኖራቸው በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ችግር ያለባቸው አካባቢዎችን መልሰን በማየት የተለየ ቆሻሻ መጣያ ቦታ እንዲመቻች ተደርጓል፡፡ ከዚህ አኳያ በሃዋሳ ከተማ ዲያስፖራ አካባቢ ያለው ቆሻሻ መጣያ አደገኛ በመሆኑ ይህን ለማንሳትና በተለዋጭ ቦታ እንዲሰራ በዚህ አመት ጥናት እና ዲዛይን ሥራ አልቆ ለኮንትራክተር የማስተላለፍ ስራው ተጠናቋል፡፡ በሌሎች ከተሞችም በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ሥራውን ለማሳለጥ “ጽዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ” የሚል ንቅናቄ መድረክ ተዘጋጅቶ በከተሞች ለውጥን የሚጭሩ በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ እንዲሁም የሰው ልጅን ክብር ማስጠበቅ ይገባል በሚል በክልሉ 80 የሚሆኑ የጎዳና ሽንት ቤቶች እየተገነቡ ይገኛል፡፡
ንጋት፦ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው የሚታየውን የጥራት ችግር?
አቶ አሻግሬ፦ የኮንስትራክሽን ትልቁ ችግር ጥራት ነው፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ የሚሰሩ ስራዎችን በቅርበት የመከታተልና የመቆጣጠር ሥራ ይሰራል። ስራዎች የህዝብን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ ዲዛይን ማድረግ፣ ዋጋቸውን ፍትሀዊ መሆኑን መቆጣጠር፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራዎችን በመስራት ግድፈቶችን ማረም እንዲሁም በግንባታው የተሰማሩ ተቋራጮችን ማብቃትና የተሻሉ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶታል።
ከዚህ ሌላ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪውን የማዘመን እና የአካባቢ ገጽታ እንዲቀየር ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡ ለዚህም የህንፃ ደረጃ በማውጣት ተግባራዊ እየተደረገ ነው፡፡ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚኖረውን አጠቃላይ የሀብት ብክነት ሊቀንስ የሚችል በቢሮ ደረጃ አደረጃጀት የመቀየር ስራ ተሰርቷል፡፡ ለአብነት ከዚህ ቀደም የግንባታ ሥራው የሚመራው በአንድ ዘርፍ ነው፡፡ ዲዛይን የማዘጋጀት እንዲሁም ጨረታ የማውጣት የመሳሰሉ ተግባራት የሚከናወኑት በአንድ ሰው ነበር፡፡ በግንባታ ሂደት ውስጥ ሊኖር የሚችል የሀብት ብክነትና ዝርክርክነት ሊያስቀር የሚችል አደረጃጀት እስከ ታች ወርዶ አንዱ አንዱን መቆጣጠር የሚችል አደረጃጀት ተፈጥሮ ሥራው እየተመራ ነው፡፡ በክልሉ መንግስት ከ 3 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ የተለያዩ ሥራዎች እየተሰሩ ሲሆን ከእነዚህም 70 በመቶ ህንፃዎች ተጠናቀዋል። ቀሪ ሥራዎች በትኩረት በመሰራት ላይ ነው፡፡
ንጋት፦ በከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥን ከማዘመን አኳያ ምን ያህል ተሰርቷል?
አቶ አሻግሬ፦ ከተሞች የአገልግሎት አሰጣጥ ሥርዓትን እንዲያሳልጡ ቴክኖሎጂን መተግበር ግድ ይላል፡፡ ከዚህ አኳያ በሀዋሳ ከተማ የመሬት አስተዳደር ስራ ዳታ ቤዝ ውስጥ የማስገባት ስራ ከ70 በመቶ በላይ አልቋል፡፡ የሀዋሳ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አገልግሎት አሰጣጥ የተበታተነውን ሰብሰብ በማድረግ ወደ አንድ ቦታ መመለስ ተችሏል፡፡
ከዚህ ሌላ ለኮንስትራክሽን ደረጃ መለየትና ፈቃድ የመስጠት ሥራን ዲጅታል ማድረግ ተችሏል፡፡ ሌሎች አገልግሎቶችን ወደ ዲጅታላይዝ በመውሰድ የስማርት ሲቲ ከተሜነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ የስማርት ሲቲ አስተሳሰብ በሁሉም የከተማ አመራር ማስጨበጥ የተቻለ ሲሆን ይህም ከተማዋን ወደ ስማርት ሲቲ ለማሸጋገር የሚያግዝ ነው፡፡
በተጨማሪም እንደሀገር የተጀመረው የኮሪደር ልማት ሀዋሳ ከተማ ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ንቅናቄ በመፍጠር ከነዋሪዎች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ የማቀጣጠያ ሰነድና እቅድ የተዘጋጅ ሲሆን በቅርቡ ይገለፃል፡፡ ይህን በማሳካት ሀዋሳ ከተማን እንደ ሀገር ተምሳሌት እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ ምርጥ ከተሞች ከሚባሉት ውስጥ አንዷ እንድትሆን የሚል እቅድ ይዘን እየሰራን ነው፡፡
ንጋት፦ በመጨረሻም ቀረ የሚሉት ሀሳብ ካለ?
አቶ አሻግሬ፦ በክልሉ የከተሞች የስበት ማእከልነት ሊያጠናክሩ የሚችሉ የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ አስተዋጽኦ ያላቸውን እንቅስቃሴዎች በሁሉም አካባቢዎች ማካሄድ ችለናል፡፡ ኢንቨስትመንት፣ የወጣቶች ሥራ እድል ፈጠራ፣ የኢንዱስትሪዎች መስፋፋትንም ጭምር ሊያሳካ የሚችል ሰፊ ስራ ተሰርቷል፡፡ ከዚህ አኳያ ሀዋሳ ከክልላችንም ሆነ ከሀገራችን ካሉ ከተሞች ሞዴል ናት፡፡
በሌላ በኩል በአንዳንድ ከተሞች የፕላን ጥሰቶች የሚታይ መሆኑ፣ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው በራሱ ተለዋዋጭ መሆኑ በሚፈለገው ልክ ከተሞች ደረጃውን ጠብቀው እንዳይሄዱና ግንባታቸው ፈጥነው ወደ ኢኮኖሚ እንዳይገቡ የማድረግ ተግዳሮት ይስተዋላል፡፡ ከዚህ ሌላ ከተሞች ራሳቸውን ችለው እንዲያድጉ ገቢያቸውን ማሳደግ በትኩረት ሊሰራ ይገባል፡፡ እነዚህን ለማስተካከልም የከተማ አመራር ስርአት ላይ ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው፡፡
በአጠቃላይ በከተማ የሚኖር ነዋሪ በከተማው የሚደረግ የልማት ርብርብ የራሱ እንደሆነ አምኖ እስካሁን ሲያደርግ የመጣውን የልማት ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠል አለበት፡፡
ንጋት፦ ለሰጡን ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ አሻግሬ፦ እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ