የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለ4ተኛ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪና ለመጀመሪያ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን   871 ተማሪዎች አስመረቀ

የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለ4ተኛ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪና ለመጀመሪያ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን   871 ተማሪዎች አስመረቀ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 27/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጂንካ ዩኒቨርስቲ ለ4ተኛ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪና ለመጀመሪያ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ያስተማራቸውን   871 ተማሪዎች አስመረቀ፡፡

ከተመራቂ ተማሪዎቹ ውስጥ ወንድ 637 ሴት 139 በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ ደግሞ በሁለተኛ ዲግሪ ሴት 16 ወንድ 69 በድምሩ 85 ተማሪዎቾ መመረቃቸው ታውቋል።

የእለቱ የክብር እንግዳና የጂንካ ዩኒቨርስቲ የስራ አመራር ቦርድ ምክትል ሰበሳቢ የሆኑት ኘሮፌሰር አሰፋ አስማረ ባስተላለፉት መልእክት የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎች በርካታ ውጣ ውረዶችን አልፋችሁ ለዚህ ክብር በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ካሉ በኋላ ተመራቂ ተማሪዎች ከትምህርት ዓለም ወደ ስራ ዓለም የምትሠማሩበት ወቅት በመሆኑ የሚያጋጥሟችሁን ፈተናዎች በብርታትና በትጋት በመጋፈጥ የሕይወት ዘመን ፈተናዎቻችሁን በብቃት መሻገር ይጠበቅባችኋል ብለዋል።

ኘሮፌሰር አሰፋ አስማረ ጨምረው እንዳሉት  ተመራቂ ተማሪዎች በሃገር እድገትና ልማት ላይ ደርሻችሁ ከፍተኛ በመሆኑ በተመረቃችሁበት የትምህርት መስክ ሕዝብና ሃገር የማገልገል አደራ ተጥሎባችኋል ሲሉም ተናግረዋል።

የጂንካ ዩኒቨርስቲ ኘሬዝዳንት ዶ/ር ኩሴ ጉዲሼ በበኩላቸው ተመራቂ ተማሪዎች  በትምህርት ዘመናችሁ ያጋጠሟችሁን ልዩ ልዩ መሠናክሎች  ተሻግራችሁ ለዛሬው የደስታ ቀን በመብቃታቾሁ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ ብለዋል።

ዶክተር ኩሴ ጉድሼ ጨምረው እንደተናገሩት ተመራቂ ተማሪዎች ከፊት ለፊት የሚገጥሟቾሁን ፈተናዎች ለማለፍ አሁኑኑ ራሳችሁን በስነ ልቦና ማጠንከር ይጠበቅባቾኋል ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል።

ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው እንደገለፁት ከትምህርት ዓለም እርቀው ወደ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ መሸጋገራቸው ልዩ ስሜት እንደሚፈጥርባቸው ገልፀው ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ በመሣተፍ ለሃገራቸውና ለሕዝባቸው የሚጠበቅባቸውን ለማከናወን ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ወንድዬ ካሳ