“የፖሊስ አገልግሎትን የማዘመን ስራ ተሰርቷል” ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ

የሳምንቱ የንጋት እንግዳችን ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ አየለ ይባላሉ፡፡ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ ናቸው፡፡ በፖሊስ ተቋም ውስጥ ለ17 አመታት አገልግለዋል፡፡ በቆይታችንም በከተማው የፖሊስ ተቋማትንና አገልግሎቶችን ለማዘመን እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን እንዲያስቃኙን ጋብዘናቸዋል፡፡

በመለሰች ዘለቀ

ንጋት፡- ለቃለ መጠይቃችን ፈቃደኛ ስለሆኑ በዝግጅት ክፍሉ ስም አመሰግናለሁ፡፡

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- እኔም ስለ ተሰጠኝ እድል አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ከትውውቅ እንጀምር እራስዎን ያስተዋወቁልኝ?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- ተወልጄ ያደኩት በሲዳማ ክልል በንሶ ወረዳ ነው። የመጀመሪያ እና 2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀኩ በኋላ እስከ መጀመሪያ ደረጃ ዲግሪ ተምሬያለሁ፡፡ የሥራ ዓለምንም በበንሳ ወረዳ በትራፊክ ባለሙያነት እንዲሁም በምርመራ ዘርፍም በማገልገል ነው የጀመርኩት፡፡ ከዛ በኋላ በተለያዩ ወረዳዎች በመዘዋወር በፖሊስ አዛዥነት አገልግያለሁ፡፡ በሀዋሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ በተለያዩ ኃላፊነቶች የምርመራ ክፍል ኃላፊ፣ የወንጀል መከላከል ዳይሬክተር፣ እንዲሁም ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የሀዋሳ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ በመሆን እያገለገልኩ እገኛለሁ፡፡

ንጋት፡- የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ አስተማማኝ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ምን ይመስላሉ?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- የሀዋሳ ከተማ ሰላምን ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡ በተለይ ከዛሬ 4 እና 5 አመት በፊት ብዙ ወንጀሎች ይከሰቱ እንደነበር ይታወቃል። ትላልቅ ዝርፊያዎች፣ ንጥቂያዎች፣ በሞተር ሳይክል የታገዙ ስርቆቶችን ጨምሮ ከፍተኛ ወንጀሎች ይከሰቱ ነበር፡፡

በተለይ ከሶስት አመታት ወዲህ ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ በትኩረት እየተሰራ በመሆኑ ብዙ ወንጀሎችን መቀነስ ተችሏል፡፡ የከተማዋ ነዋሪ በወንጀል መከላከሉ ስራ ላይ ድርሻ እንዲኖረው ህብረተሰቡን የሚወክሉ ገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤቶችን የማደረጀት ስራ ተሰርቷል፡፡ እነዚህ ገለልተኛ አማካሪ ምክር ቤቶች ከክፍለ ከተማ እስከ ቀበሌ ድረስ የፖሊስን ስራ የሚገመግሙ የህብረተሰቡ ተወካይ ናቸው። በቅርቡ በአዲስ መልክ ወደ ስራ የገባው የገለልተኛ አማካሪ ቡድን በ8ቱም ክፍለ ከተሞች ፖሊስ ውጤታማ ተግባራትን እንዲያከናውን አስችሎታል፡፡ በሕብረተሰብ ተሳትፎ ሰፋ ያሉ ተግባራትን ካከናወኑ ክፍለ ከተሞች መካከል የመሃል ከተማ ክፍለ ከተማ ተጠቃሽ ነው፡፡

ሌላው የፓትሮል ቅኝት አባላትን በብሎክ፣ በመንደርና በቀበሌ ደረጃ በመመደብ የቀንና የማታ የሮንድ ስምሪት እንዲሰራ ማደራጀትና የማሰልጠን ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ለጸጥታ አጋዥ ሊሆኑ የሚችሉ የሰላም አምባሳደሮችን የጸጥታ አካል በማድረግ በተለይ ትላልቅ መንፈሳዊና መንግስታዊ ስብሰባዎች ሲኖሩ አጋዥ አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ሥራዎች ተሰርተዋል፡፡ በዚህም ትላልቅ በዓላቶች ሲከበሩ ከጸጥታ ሀይሉ ጎን ሆነው ፍተሻን ጨምሮ ጥበቃንም ሊያግዙ የሚችሉ የሰላም አምባሳደር ወጣቶች እንዲመለመሉ ተደርጓል፡፡ ከእነዚህ አካላት ጋር በጋራ በመስራት ወንጀሎች እንዲቀንሱ የማድረግ ስራዎች ተከናውነዋል፡፡

እያንዳንዱ አካባቢ በተለይ የግል ተቋማትና ድርጅቶች አካባቢ ላይ ቋሚ፣ የሰለጠና ከፖሊስ ጋር ሊተባበር የሚችል ጥበቃ መቅጠር እንዳለባቸው ከስምምነት ተደርሶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ ከዚህ የተነሳ ሀዋሳ ከተማ ዛሬ ላይ ሰላም የሰፈነባት ከተማ ሆናለች ማለት ይቻላል፡፡

ንጋት፡- በዚህ ሂደት የተያዘ አጥፊዎች ከማስተማር አንፃር የተሰራ ሥራ ይኖር ይሆን? ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- በተደጋጋሚ በወንጀል ተሳትፎ የተጠረጠሩ አካላትን የመለየት ስራና ፖሊስ በሚያቀርባቸው ማስረጃ ላይ ተመስርቶ አቃቤ ህግና ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲሰጡ በማድረግ አስተማሪና ተመጣጣኝ እርማት እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ታርመው ሲወጡም በትክክል ስለመታረማቸው “የተሻሻሉ አልያም በጥፋት ተግባሩ ላይ የቀጠለ ማን ነው?” በሚል የመለየት ስራ ተሰርቷል፡፡

በሌላ በኩል የወንጀል ተግባር ስጋት ናቸው የተባሉ ቦታዎች ላይ ከማህረሰቡ ጋር በተደረገው ውይይት ከተማዋን ሊመጥን የሚችል የፖሊስ ማዕከላት እንዲገነቡ ተደርጓል፡፡ በተደጋጋሚ ወንጀል ሲፈጸሙ የነበሩ ቦታዎችን በመለየት በህብረተሰቡ ተሳትፎ በከፍተኛ ወጪ ከ40 በላይ ማዕከላትን መገንባት ተችሏል፡፡

ከዚህም ባሻገር በሶስት ክፍለ ከተሞች ላይ የፖሊስ ጣቢያ ግንባታ ተጀምሯል፡፡ ከ336 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት የተደራጁ የፖሊስ ጣቢያዎች እየተገነቡ ይገኛሉ፡፡

ንጋት፡- የፖሊስ አገልግሎትን ለማዘመን የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለጻሉ?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- የወንጀል መከላከሉን ተግባር ዘመናዊ ከማድረግ ረገድ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡ በተለይ የወንጀል መከላከሉ ተግባር በፖሊስ ብቻ የሚደረግ ክትትል በቂ ባለመሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ወንጀል ለመከላከል በከተማዋ ብዙ ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሀዋሳ ከተማ ላይ የመንገድ ላይ ካሜራዎች እንዲገጠም ተደርጓል፡፡

አብዛኛው ወንጀል ይከሰትባቸዋል ተብሎ በተለዩ ቦታዎች ላይ የተተከሉ ካሜራዎችን ለ24 ሰዓት የሚከታተሉ ፖሊሶችን በመመደብ ወንጀሎች ሲፈጸሙ እጅ ከፍንጅ እንዲያዙ የማድረግ ስራ እየተሰራ ነው፡፡

የንግድ ድርጅቶች፣ አልጋ ቤቶች፣ የመዝናኛ ስፍራዎች ጭምር ካሜራ እንዲገጥሙ ተደርጓል። በዚህም በከተማ ውስጥ ከ441 በላይ የሚሆኑ ድርጅቶች የራሳቸውን ካሜራ እንዲተክሉ ተደርጓል፡፡ የከተማ ነዋሪ ወንጀልን ለመከላከል በሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የራሱን ድርሻ እንዲወጣ በማድረግ ወንጀልን በዘመናዊ መንገድ ለመከላከል አዲስ ሶፍት ዌር ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ተገብቷል። በአሁኑ ጊዜ በየትኛውም አልጋ ቤት የሚያድር ሰው ድጅታል በሆነ መልኩ ተመዝግቦ በሶፍት ዌር አማካኝነት ከፖሊስ ጋር እንዲገናኝ ተደርጓል፡፡

እነዚህን ተግባራት በማከናወን የወንጀል ተግባራትን ለመከላከል በትኩረት ከሚሰራው ሥራ ጐን ለጐን እየተሰራ ነው። ወንጀል ሲፈጸም ደግሞ ለፖሊስ ቶሎ መረጃ ሊደርስ የሚችልባቸው አማራጮች ፈጥረናል፡፡

ለዚህም የሀዋሳ ከተማ ፖሊስ 7614 የሚባል ነጻ የፖሊስ ስልክ መስመር አዘጋጅቷል። ማንኛውም ሰው የት ሆኖ እንደሚደውል ይታወቃል፡፡ ወዲያው አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኝ ይደረጋል። በዚህም አራትና አምስት ሰዎችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ ይችላል፡፡ ችግሮች እንኳን ቢከሰቱ የስልክ መጨናነቅ ሳይኖር በተመሳሳይ ሰዓት በርካታ ባለጉዳዮችን ማስተናገድ ይቻላል፡፡

ይህንን አገልግሎት ሊያሳወቅ የሚችል ማስታወቂያ ከተማ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ ተሽከርካሪዎች ላይ 7614 ለተሳፋሪ ሊታይ በሚችልበት ቦታ ላይ ተለጥፏል፡፡

ሌላኛው ማህበረሰቡ ስለ ወንጀል አስከፊነት እንዲወያይ የማድረጉ ስራ ነው፡፡ በተለይም በዓላቶችና ፕሮግራሞች ሲኖሩ ቀድሞ ህብረተሰቡ እንዲወያይ እናደርጋለን፡፡ ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከተማ አስተዳደር ባሉ መዋቅሮች ላይ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡ በዚህም የወንጀል መከላከሉ ስራዎች እጅግ ውጤታማ ሆነዋል ማለት ይቻላል፡፡

ንጋት፡- የትራፊክ አገልግሎትን ለማቀላጠፍ ምን ምን ስራዎች ተሰርተዋል?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- ከወንጀል መከላከል ባሻገር ፖሊስ ተቋም ከሚያከናውናቸው ተግባራት አንዱ የትራፊክ አገልግሎት ነው፡፡ ከዚህ በፊት በተለይ በሞተር ሳይክል ተሽከርካሪ ጋር ተያይዞ አደጋዎች ይከሰቱ ነበር፡፡ በከተማ ውስጥ በእግረኞችና ላይ ይደርሱ የነበሩ አደጋዎችን በተወሰነ መልኩ መቀነስ ተችሏል፡፡ በትምህርት ቤቶች የትራፊክ ትምህርት እንዲሰጥ ተደርጓል። ተማሪዎች የሰንደቅ አላማ ስነ ስርዓት ሲፈጽሙ መንገድ እንዴት ማቋረጥ እንዳለባቸው፣ እርስ በርሳቸው ደግሞ ስለ ትራፊክ መማማር እንዲችሉ ትራፊክ ክበባትን በማደራጀት የትራፊክ አደጋዎችን የመከላከል ስራዎች ላይም በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በመናኸሪያዎች፣ በገበያዎች እና ሰው በሚበዛባቸው አካባቢዎች የተለያዩ ብሮሸሮችን በማዘጋጀት ስለ ትራፊክ አደጋ አስከፊነት ትምህርት እየተሰጠ ነው፡፡ ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ ከሞተር ሳይክሎች ጋር ተያይዞ ከህግና ስርዓት ውጪ በሚያሽከረክሩና ትርፍ በሚጭኑት ላይ ተመጣጣኝ ቅጣት በመጣል መስመር ውስጥ እንዲገቡ ይደረጋል፡፡ ከትራፊክ ስነ-ምግባር አንጻርም የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ትራፊኮች የሚሰሯቸውን ስራዎች ማየት በሚችልበት ቦታዎች ላይ ካሜራዎችን የመግጠም ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ትራፊኮች የሚያደርጉትን ቁጥጥር ለህብረተሰቡ ግልጽ እንዲሆን የማድረግ፣ የስነ ምግባር ችግር ያለባቸውና ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚቀርብባቸው ትራፊኮችን የማረምና እርምጃ የመውሰድ ስራ ተሰርቷል፡፡

ንጋት፡- የወንጀል ምርመራ አገልግሎት አሰጣጥን ውጤታማ ለማድረግ የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- ተቋሙ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች አንዱ የወንጀል የምርመራ አገልግሎት ነው፡፡ የወንጀል ምርመራ ስራዎቻችንም ቀድሞ ከነበረው ችግር ለማላቀቅ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው፡፡ ይህንን ለማዘመን መርማሪና ቅሬታ አቅራቢው ወይም ቃል ሰጪው ግልጽ በሆነ ሁኔታ ላይ እንዲስተናገዱ በክፍሉ ካሜራ ተገጥሞ ግልጽ በሆነ ሁኔታ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ ተገልጋዩ በቀጠሮ እንዳይመላለስ ፈጣን አገልግሎት እየተሰጠ ነው። ቅሬታ ሲኖር ደግሞ በማጣራት መፍትሄ እንዲያገኝ ይደረጋል፡፡

በስነ ምግባር የተመሰገነና ለህብረተሰቡ ታማኝ የሆነ ፖሊስ እንዲፈጠር በአባላት የሚታዩ ክፍተቶችን በመገምገምና በማረም የሚሰጠውን አገልግሎት ግልጸኝነት ያለው እንዲሆን እየተሰራ ይገኛል፡፡

ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ የፖሊስ ተቋማትን በማዘመን የህብረተሰቡን አመኔታ ከፍ ለማድረግ እየተሰራ ነው፡፡

ንጋት፡- በአሁኑ ጊዜ የከተማዋ የጸጥታ ሁኔታ ምን ይመስላል?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- በሀዋሳ ለ24 ሰዓት ሰዎች የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች አሉ። ከተለያዩ ከሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ የሚመጡ እንግዶች የእረፍት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉና ሊዝናኑ የሚመርጧት ከተማ ናት፡፡ በርካቶች ለኑሮና ለጉብኝትም የሚመኟት፤ የቱሪዝም ከተማ እንደመሆኗ መጠን የከተማዋን ዕድገት የሚመጥን የፖሊስ ቁመና ለመገንባት በርካታ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

ከዚህ የተነሳ ከተማችን የሰላም ቀጠና ሆናለች ማለት ይቻላል፡፡ ሆኖም ግን አንዳንድ አካላት በግል ሚዲያዎቻቸው ላይ የከተማዋን ገጽታ ሊያበላሽ በሚችል ሆኔታ ከተማዋ ሰላም እንዳልሆነች ሲዘግቡ ይታያሉ፡፡ እነዚህ አካላት በህግ እንዲጠየቁ ተደርጓል፡፡

ንጋት፡- የከተማዋን ሰላምና ጸጥታ ለማስጠበቅ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የመስራት ተግባር ምን ይመስላል?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- ከአቃቤ ህጎች፣ ከፍርድ ቤቶች፣ ከትራንስፖርት ቢሮ፣ ከንግድ ቢሮ፣ እንዲሁም ከሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ እና ማዘጋጃ ቤቶች ጋር በቅንጅት እንሰራለን። የሀዋሳ ከተማ ሰላም የበርካታ አካላት ድካምና ልፋት ውጤት ነው፡፡ በአጠቃላይ ማህበረሰቡና የህግ አካላትና አመራሩም ጭምር ለከተማዋ ሰላም የበኩሉን እየተወጣ ነው፡፡

ንጋት፡- በከተማዋ የወንጀል ስጋት ናቸው ተብለው የተለዩ ተግባራት ምን ምንድን ናቸው?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- ወንጀል ተለዋዋጭ ባህሪ አለው፡፡ ከጊዜውም ጋር ተያይዞ ተለዋዋጭነቱ በዛው ልክ ነው የሚሆነው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ህብረተሰቡን በማደናገር የሚፈጸሙ ወንጀሎች አሉ፡፡ አልፎ አልፎ በሞተር የታገዘ ንጥቂያዎች ነበሩ፡፡ ይህም በተጠናከረ ክትትልና እርምጃ በአሁኑ ጊዜ ቀንሷል ማለት ይቻላል፡፡

ለአብነትም በዚህ አመት በሞተር ሳይክል የነበሩ ወንጀለኞች ለመቆጣጠር ከተለያዩ ግለሰቦች ሞባይል ሲነጥቁ በተደረገው የካሜራ ክትትልና የተጠናከረ ኦፕሬሽን ስራ ተጠርጣሪውን ከነሞተሩ በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል፡፡ የምርመራ መዝገቡን ፖሊስ በተገቢው አጣርቶ ለሚመለከተው የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ዐቃ ህግ አስተላልፏል፡፡

መዝገብ የደረሰው የሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ዐቃቤ ህግ መዝገቡን ከተመለከተ በኋላ በሀዋሳ ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፋይል አስከፍቷል፡፡

አቃቤ ህግ የቀረበውን የሰነድና የሰው ማስረጃ በሚገባ የመረመረው ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በቀረበበት አንቀፅ ስር ጥፋተኛ ሆኖ በመገኘቱ ተጠርጣሪው በ3 ዓመት ከ3 ወር ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል።

ንጋት፡- የሚሉት ሃሳብ ካለ አንስተው መልዕክቶዎን ቢያስተላልፉ?

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- ወንጀሎች ሲከሰቱ ህብረተሰቡ በመተባበር ለህግ በማቅረብና ጥቆማ በመስጠት የወንጀል ቀጠናዎችን ለፖሊስ ማሳወቅ መቻል አለበት፡፡ ለምሳሌ ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን፣ ኮንትሮባንዶችን እንዲሁም የሺሻ ቤቶችን መጠቆም የህብረተሰቡ ኃላፊነት ነው። የከተማዋ ነዋሪዎች በሞተር በሚንቀሳቀሱበት ወቅት እያሽከረከሩ ስልክ ማናገር ለከፋ አደጋ ጭምር የሚያጋልጥ በመሆኑ ከአደጋው መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡

በሌላ በኩል ሰላም የሚመጣው በጸጥታ አካል ጥረት ብቻ ሳይሆን በህብረተሰቡ ርብርብና አብሮ በመስራት ነው፡፡ በመሆኑም ህብረተሰቡ ከጸጥታ ሀይል ጋር አብሮ መስራትና ከተለያዩ የወንጀል ስጋቶች ራሱን እንዲጠብቅ መልዕክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

ንጋት፡- ፈቃደኛ በመሆን ስለሰጡኝ ማብራሪያ በዝግጅት ክፍሉ ስም በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡

ምክትል ኢንስፔክተር መልካሙ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡