በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከ103 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሰኔ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በወላይታ ዞን በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከ103 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ፡፡

በወላይታ ዞን በዘንድሮ አረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ከ103 ሚሊዮን በላይ ችግኝ ለመትከል ታቅዶ እየሰራ እንደሚገኝ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ክፍሌ ታውሌ ገልጸዋል።

በ2016 በጀት ዓመት በ305 ችግኝ ጣቢያዎች 99 ነጥብ 1 ሚሊዮን የተለያዩ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ ከ103 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ ችግኝ መዘጋጀቱን አቶ ክፍሌ አስረድተዋል።

በበልግ 35 ሚሊዮን ችግኝ ለመትከል ታቅዶ 36 ነጥብ 2 ሚልዮን መተከሉን የገለጹት ኃላፊው በመኸር 50 ሚሊዮን እና በአንድ ጀምበር 23 ሚሊዮን ዘርፈብዙ ጠቀሜታ ያላቸውን ለመትከል መታቀዱንም አስታውቀዋል፡፡

ለዚህም ቅድመ ዝግጅት ሥራዎች የችግኝ ዝግጅት፣ የተከላ ቦታ ዝግጅት፣ የካርታ ሥራ፣ የተከላ ጉድጓድ ዝግጅት፣ ኮምፖስት ዝግጅት፣ የተሳታፊ የሰዉ ኃይል ልዬታ ስራ መሰራቱንም ኃላፊው ገልጸዋል።

ለሰው ልጆች ምቹ የመኖሪያ ስፍራ ለመፍጠር፣ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚደረገው ጥረት እንዲሳካና ያልተበከለ አየር ለመተንፈስ ችግኝ መትከልና መንከባከብ ሁነኛ መፍትሔ እንደሆነም አስገንዝበዋል።

ህብረተሰቡ ከዚህ በፊት በየአካባቢው የተተከሉ ችግኞች ዛሬ ላይ የሚሰጡትን ጠቀሜታ በማገናዘብ ለአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ ክፍሌ ታውሌ፣ የወላይታ ዞን ደንና አከባቢ ጥበቃ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ መርክነህ ማለዳን ጨምሮ ሌሎች የዞኑ ከፍተኛ አመራሮች የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ዘጋቢ፡ በቀለች  ጌቾ  – ከዋካ  ቅርንጫፍ