በስልጤ ዞን የሚገኘው ሃይረንዚ ልዩ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በ2017 የትምህርት ዘመን በሃገር አቀፍ ብሔራዊ ፈተና ላይ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና ውጤቱ እንዲመዘገብ አስተዋጽኦ ላደረጉ መምህራን የማትጊያና የእውቅና ፕሮግራም ተካሄደ
በማትጊያና እውቅና ፕሮግራሙ ላይ የተገኙት የስልጤ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘይኔ ቢልካ፤ ዞኑ ለትምህርት ልማት በሰጠው ልዩ ትኩረት ከቅድመ መደበኛ እስከ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ ከ280 ሺህ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የትምህርት ስራውን ውጤታማ ለማድረግም የዞኑ ባለሃብቶችና የብሔረሰቡ ተወላጆች ከ330 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል።
በዞኑ የሚገኘው ሃይረንዚ ልዩ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተከታታይ አመታት ያስመዘገበው የተማሪዎች ውጤት በጋራ መስራት ከተቻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።
ይህንን ውጤታማነት በሁሉም የዞኑ ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ ለማድረግና ሂደቱ ቀጣይነት እንዲኖረው መስራት እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ዋና አስተዳዳሪው በ2017 የትምህርት ዘመን ውጤት አምጥተው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለሚገቡ ተማሪዎች መልእክታቸውን ያስተላለፉ ሲሆን ትምህርት የእድሜ ልክ ጉዞ እንደመሆኑ ለዚህ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የስልጤ ልማት ማህበር ስራ አስፈጻሚ ጨቶ ሸምሲ ኑሪ በበኩላቸው፤ በ2017 የትምህርት ዘመን 105 ተማሪዎችን በማስፈተን ሙሉ ለሙሉ ማሳለፉንና አማካይ ውጤቱም እየተሻሻለ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በእለቱ ልዩ ትምህርት ቤቱ ከተመሰረተበት ከ2007 ዓ.ም ጀምሮ እያከናወናቸው የመጡ ተግባራት ሪፖርት ቀርቧል።
በእውቅና ፕሮግራሙ የዞኑ የሚመለከታቸው አካላት፣ የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን ጨምሮ የክልል እና የፌደራል እንዲሁም የዞኑ ተወላጅ ባለሃብቶች ተሳታፊ ሆነዋል።
በመርሃ ግብሩ ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች እና መምህራን የማትጊያና የእውቅና ሽልማት የሚበረከትላቸው ይሆናል።
ዘጋቢ: ወንድወሰን ሽመልስ
More Stories
የዋካ ቅርንጫፍ ጣቢያ ወቅታዊና ጥራት ያለውን መረጃ ተደራሽ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በላቀ ደረጃ እንዲወጣ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ
የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጉዞ እውን እንደሚሆን በግብርናው ዘርፍ እየተሰሩ ያሉ ውጤታማ ስራዎች ማሳያ ናቸው – ሚኒስትር አዲሱ አረጋ