ፅዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፋ የንቅናቄ መድረክ በአሪ ዞን በጂንካ ከተማ ተካሄደ

ፅዱ ከተሞች ለኢትዮጵያ ከፍታ በሚል መሪ ቃል ከተማ አቀፋ የንቅናቄ መድረክ በአሪ ዞን በጂንካ ከተማ ተካሄደ

በዉይይቱ ላይ የጂንካ ከተማ ነዋሪዎችና ተጋባዥ የክብር እንግዶች የተገኙ ሲሆን ዉይይቱም በ32 ከተሞች የሚካሄድ ልዩ የሆነ የንቅናቄ መድረክ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሰናይት ሰለሞን በመክፈቻ ንግግራቸው ገልፀዋል።

አያይዘዉ ከተሞች ያለ ነዋሪዉ ህዝብ ተሳትፎ መልማትና ዉብ መሆን እንደማይችሉ ጠቁመዉ ፅዱና ዉብ የሆኑ ከተሞች ለንግድ፣ ለኑሮ፣ ለኢንቨስትመንት፣ ለቱሪዝም ተመራጭ መሆናቸዉን ተናግረዋል።

የጂንካ ከተማ የቱሪዝም ማዕከል እንደመሆኑ ከተማዉን ዉብና ጽዱ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ተወዳዳሪና ተመራጭ ከተማ እንዲሆን የሁሉንም የነቃ ተሳትፎ ይጠይቃል ብለዋል።

በዉይይቱ ህብረተሰቡ ቆሻሻን ያለአግባብ ዉጪ መጣል፣ የዉሃ መፋሰሻ ዲቾች መደፈን፣ በማዘጋጃ ቤት በኩል ቁጥጥር እና ክትትል ማነስ፣ ቆሻሻ መጣያ ቦታ በማዘጃ ቤት በኩል አለመዘጋጀት፣ የከተማዉ የዉስጥ ለዉስጥ መንገድ በአግባቡ ያልተሠራ መሆን እና ቆሻሻን በየቦታዉ በሚጥሉ ሰዎች ላይ ተመጣጣኝ እርምጃ አለመውሰድ እና ለሎች የተለያዩ ችግሮችን ተሳታፊዎቹ አንስተዋል።

የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ አስፋዉ ዶሪ በተለያየ አካባቢ ሆነን የምናካሂደዉ የአካባቢ ፅዳትና ውበት ለኢትዮጵያ ከፍታ ያለዉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዉ፤ በአካባቢ ፅዳትና ውበት ላይ የመንግስትና የህብረተሰቡ በጋራ መስራት ያለዉ ድርሻ የጎላ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በአካባቢ ፅዳትና ዉበት፣ በአፈር እና ዉሃ ጥበቃ ሥራ፣ ተራራዎችን መጠበቅ እና ማልማት እንዲሁም ጂንካ ከተማን ማልማት፣ ከህብረተሰቡ ይጠበቃልም ብለዋል።

በቀጣይ ህብረተሰቡ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች ትኩረት ተሰጥቶ የሚሠራ መሆኑንም ከንቲባው አስረድተዋል።

የዞኑ የብልፅግና ፓርቲ ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በየቀጠናዉ በአረንጓዴ ልማት ቦታዎች ላይ ቤት፣ ትምህርት ቤቶች፣ የሀይማኖት ተቋማት፣ ያለአግባብ እየተሠሩ ስለሆነ እነዚህን ቦታዎች መንግስት፣ ባለሀብቶች እና ግለሰቦች መጠበቅ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ቆሻሻን መልሶ በመጠቀም ዙሪያ ቀጣይ ግንዛቤ እየተፈጠረ ይሄዳል ያሉት ኃላፊው በዚህ ዙሪያም ማህበራትን በማጠናከር እንዲሠሩ እና የከተማዉ ቆሻሻ ማጠራቀሚያ እየተመቻቸ ይሄዳል ብለዋል።

በመድረኩ የመወያያ ሰነድ ቀርቦ ሰፊ ወይይት ከተካሄደ በኋላ በኔሪ መለስተኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ተምህርት ቤት የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር ተካሂዷል፡፡

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን