የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ ያለውን የትራፊክ አደጋ ለመከላከል የሁሉንም ዜጋ ትብብር እንደሚጠይቅ ተገለጸ
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትራንስፖርትና የመንገድ ልማት ቢሮ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ያለመ ንቅናቄ በአርባምንጭ ከተማ እያካሄደ ነው።
በማስጀመሪያ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት በክልሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ሀላፊ እንዲሁም የክልሉ ርዕስ መስተዳድር ተወካይ አክሊሉ አዳኝ እንደገለፁት የትራፊክ አደጋ ሰብዐዊ እና የንብረት ውድመቱ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ በጋራ ጥረት መገታት አለበት ብለዋል።
መንግስት ይህን ችግር ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው ያሉት አቶ አክሊሉ የመንጃ ፍቃድ ማሰልጠኛ ተቋማትን መቆጣጠር፣ ያጠፉትን ማረምና የተሻለ አፈፃፀም ያላቸውን ማበረታታት፣ የተሽከርካሪዎችን ብቃና ይዞታ መቆጣጠር፣ የትራፊክ ፍሰቱን ስርዐት ዘመናዊ እና በቴክኖሎጂ የተደገፈ ማድረግ እየተሰሩ ካሉ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
የክልሉ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ሀላፊና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ሀላፊ ተወካይ አቶ ዘብዲዮስ ኤካ እንደገለፁት የትራንስፖርት ዘርፉ በአግባቡ ካልተያዘ ለሀገር ብልፅግና እንቅፋት ነው።
ኢትዮጵያ ያሏት ተሽከርካሪዎች በአንፃራዊነት በቁጥር አናሳ ናቸው ያሉት አቶ ዘብዲዮስ የምናስተናግደው የትራፊክ አደጋ ግን ከፍተኛ በመሆኑ መገታት አለበት ብለዋል።
በኢትዮጵያ ብሎም በክልሉ በትራፊክ አደጋ የበርካቶችን ህይወት እየቀጠፈ የሀገር ሀብትን ደግሞ እያወደመ ቀጥሏል። ይህን ችግር ከምንጩ በመለየት ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ሁሉም ዜጋ የበኩሉን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተያዘው አመት ብቻ 152 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን ያጡ ሲሆን የንብረት ውድመቱ ከ13.3 ሚሊየን ብር በላይ ሰለመሆኑ ከክልሉ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
የኢፌዲሪ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ በርኦ ሀሰን በበኩላቸው የትራፊክ አደጋ ዜጋንና ንብረትን እየበላ ነው ብለው የክልሉ ህዝቦች የክልሉን ሰላም ለመጠበቅ ያሳዩትን ተምሳሌታዊ ተግባር በትራፊክ አደጋ እየደረሰ ያለውን ኪሳራ ለመከላከል እንዲጠቀሙም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በንቅናቄው መድረኩ ላይ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፀሀይ ወራሳን ጨምሮ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እና የሀገር ሽማግሌዎች፣ የትራፊክ ደህንነት አካላትና ተማሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
ዘጋቢ: ጀማል የሱፍ
More Stories
ጤና ጣቢያው እየሰጠ ባለው አገልግሎት መደሰታቸውን ተገልጋዮች ተናገሩ
የሰላምና የመከባበር ባህልን ለማስቀጠል የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ሚናው ከፍተኛ እንደሆነ ተገለፀ
የግብርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ኑሮ ማሻሻል እንደሚገባ ተገለጸ