በአርብቶ አደሩ ፍትሐዊ ማህበራዊ የልማት ተጠቃሚነት ላይ ተግዳሮት እየሆኑ የሚገኙ ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮችን ለይቶ አፋጣኝ መፍትሄ ለማበጀት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በአርብቶ አደሩ ፍትሐዊ ማህበራዊ የልማት ተጠቃሚነት ላይ ተግዳሮት እየሆኑ የሚገኙ ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮችን ለይቶ አፋጣኝ መፍትሄ ለማበጀት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ አስታወቀ

በቆላማ አካባቢዎች ከመሰረተ ልማት ተቋማት ዝርጋታ ባሻገር ተወዳዳሪና በቁ የሰው ሃይል የማልማት ስራም አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባም ነው የተመላከተው።

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታትም የህዝብ አስተያየቶችን በግብአትነት ያሰባሰበ መድረክ በቱርሚ ከተማ ሲካሄድ የክልሉ ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላትን ጨምሮ በየደረጃው የሚገኙ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ተወካዮችና አመራሮች ሰፊ ውይይት አካሂደዋል።

በተለያዩ ማህበራዊ የልማት ተቋማት ፈታኝ እየሆኑ የሚገኙ ችግሮች በዝርዝር ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን በተለይም በትምህርቱ ዘርፍ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ውስንነት አጽንኦት ተሰጥቶታል።

የክልሉ መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ሐብቴ በአርብቶ አደሩ ፍትሐዊ ማህበራዊ የልማት ተጠቃሚነት ላይ ተግዳሮት የሚሆኑ ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በመለየት አፋጣኝ መፍትሄ ለማበጀት የተቀናጀ ስራ መስራት እንደሚገባ ጠቅሰው በተለይም በትምህርት ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ የሆኑ የአርብቶ አደር ልጆችን የማፍራቱ ስራ በትኩረት እየሰተራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በማህበራዊ የልማት ተቋማት የጥራት ችግሮች መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው በተለይም በአዳሪ ትምህርት ቤቶች ከበጀት አንስቶ እስከ መዋቅራዊ አደረጃጀት ያሉ ውስንነቶች ተማሪዎቹ ትምህርታቸው ላይ ብቻ አተኩረው ውጤታማ እንዳይሆኑ እያደረገ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

እነዚህንና መሰል ችግሮችንም በመስክ ምልከታና ከማህበረሰብ አስተያየቶች ግብአት በመውሰድ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማበጀት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የግብርናና ገጠር ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጠንክር ጠንካ በበኩላቸው በክልሉ በሚገኙ ወደ ሰባት አዳሪ ትምህርት ቤቶች የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን ለመፍታት ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለመስራት ከመግባባት ላይ መድረሳቸውን ገልፀዋል።

በታዘብናቸው ተቋማት ለተማሪዎች ቲቶሪያል ከመስጠት ጀምሮ በተወሰኑ አካባቢዎች ለችግሮች አካባቢያዊ መፍትሔ ለመሰጠት የሚደረጉ ጥረቶች በጥንካሬ የሚገለጹ ናቸው ያሉት ሰብሳቢው በዋናነት በሁሉም ተቋማት የግብአት ችግሮችን በማሟላት ተቋማቱን የብቁ ዜጎች መፍለቂያ ማድረግ እንደሚገባ አስምረውበታል።

ለአዳሪ ትምህርት ቤቶች የተማሪ የምልመላ ሥርዓቱን ከማጠናከር ጀምሮ በየደረጃው ያለውን የማህበረሰብ ተሳትፎ በማሳደግ የተማሩ የአርብቶ አደር ልጆች የሆኑ ባለሙያዎችና አመራሮች ሚናቸውን ሊያሳድጉ እንደሚገባም በመድረኩ አስተያየቶች ሲሰነዘሩም ተደምጠዋል።

ዘጋቢ: ከተማ በየነ – ከጂንካ ጣቢያችን