አገራዊ በእናቶች፣ ህፃናትና ወጣቶች ጤና ላይ ያተኮረ የ2016 በጀት ዓመት ዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈፃፀም የግምገማና የምክክር መድረክ በአርባምንጭ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
የኢፌዲሪ የጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ዶ/ር መቅደስ ዳባ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት የቅድመ ወሊድ አገልግሎት ለእናት እና ህፃናት ወሳኝ በመሆኑ በዘርፉ የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለማረም ጠንክሮ መስራት ያስፈልጋል።
በወሊድ ወቅት የሚከሰት ሞትን ለመቀነስ ታቅዶ እየተሠራ እንደሆነ ያወሱት ሚኒስትሯ ባለፉት 3 አስርት አመታት የተመዘገበው ለውጥ የሚበረታታ መሆኑን አክለዋል።
የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት አፈጻጸም ከቦታ ቦታ የተለያየ መሆኑን ገልጸው ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ክልሎችን በመደገፍ በዘርፉ የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ ርብርብ ሊደረግ ይገባልም ብለዋል።
የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር ሚኒስቴር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ በበኩላቸው የእናቶች ማቆያ ከማስፋፋት አንፃር በሁሉም ክልሎች ጥሩ ጅምር ስራዎች እንደሚስተዋሉ ጠቁመው ይህም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።
በጤና ተቋም የሚወልዱ እናቶች ቁጥርን 90 ከመቶ ለማድረስ ታቅዶ 70 ከመቶ መከናወኑንና በቀጣይም በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በክልሉ 17 አዲስ የእናቶች ማቆያ መገንባታቸውንና 167 ነባር ማቆያዎች መጠገናቸውን ገልፀዋል።
አክለውም የመጀመሪያ 3 ወራት የቅድመ ወሊድ አገልግሎትና የክትባት ስራዎች በቀጣይ በትኩረት የሚሰሩ ይሆናሉ ብለዋል።
የስነ-ተዋልዶ፣ የእናቶች፣ የወጣቶችና የጨቅላ ህፃናት አገልግሎት የበጎነት ፈቃደኞች አምባሳደር አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ የእናቶችና የጨቅላ ህፃናት ሞትን ለማስቀረት በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአፍላ ወጣቶች ተወካይ የሆነው ወጣት ቶፊቅ እስማኤል በመድረኩ መልዕክት አስተላልፏል።
ዘጋቢ፡ ተስፋዬ አሰፋ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ