ምስራቅ አፍሪካን ያመሰው ክስተት
በኢያሱ ታዴዎስ
በየመንደሩ ሰዎች ተደናግጠው ከወዲህ ከወዲያ ይተረማመሳሉ፡፡ አንዳንዶች ከጉልበታቸው በላይ የደረሰውን ጎርፍ በእግራቸው እየገፉ ለፍተው ያካበቱትን ጥሪት ለማዳን ይጣደፋሉ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ አስከፊው ጎርፍ፣ አደጋ እንዳያደርስ አቅማቸው የደከሙትን ለማዳን ይፍጨረጨራሉ፡፡
ይህ ሁሉ እየሆነ ያለው በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ነው፡፡ ከባድ ዝናብ በመጣሉ ምክንያት ነዋሪውን ስጋት ውስጥ የጣለ ጎርፍ አስከትሏል፡፡ በመዲናዋ አከታትሎ የጣለው ዝናብ በአቅራቢያ ያሉ ወንዞችና ውሃ ማፋሰሻ ቦዮች ከመጠን በላይ ጢም ብለው ከተማዋን እንዲያጥለቀልቅ አድርጓል፡፡
መንገዶች ሁሉ በውሃ ተሸፍነዋል፡፡ ቤቶችም የጎርፍ ሲሳይ ሆነዋል፡፡ በርካታ ቤቶች ፈራርሰዋል፡፡ የጎርፉ ሙላት ከመግነኑ የተነሳ አንድም ነጻ መቆሚያ ስፍራ ማግኘት ከባድ ሆኗል፡፡
በእርግጥ በናይሮቢ የጎርፍ ሙላት ሲከሰት ይህ የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም፡፡ የጎርፍ አደጋም ቢሆን መልሶ መላልሶ ጎብኝቷታል፡፡ የአሁኑ ግን የከፋ ነው፡፡ ከተማዋ ብቻ ሳትሆን በሀገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ አካባቢዎች የጎርፍ አደጋ ተከስቶባቸዋል፡፡
ይህ ሰሞንኛው አሳዛኙ ክስተት ምስራቅ አፍሪካዊቷን ሀገር በእጅጉ አሳስቧታል። ከፈረንጆቹ ሚያዚያ 18/ 2024 ጀምሮ በሀገሪቱ የጣለው ከባድ ዝናብ በተለያዩ የኬኒያ አካባቢዎች ከቁጥጥር ውጭ የሆነ የጎርፍ አደጋ አስከትሏል፡፡ ይህም ለበርካታ ዜጎች ሞት እና መፈናቀል ምክንያት ሆኗል፡፡
በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ከሰሞኑ የሀገሪቱን አደጋ መከላከል ማዕከል ጠቅሶ ባወጣው ሪፖርት መሰረት በመላው ሀገሪቱ 205 ሺህ ሰዎች የጎርፍ አደጋው ተጠቂ ሆነዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ 228 ሰዎች ለሕልፈት ሲዳረጉ፣ 164 ሰዎች ተጎድተዋል። 72 ሰዎች የገቡበት አልታወቀም፡፡ 194 ሺህ 305 ሰዎች ደግሞ ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ “ሙራንጋ” እና “ናኩሩ” በተባሉ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከፍተኛ የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከስቶ ነበር፡፡ በናኩሩ በተከሰተው አደጋ 52 ሰዎች ሕይወታቸውን እንዳጡ ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በሀገሪቱ 9 ሺህ 712 ሄክታር መሬት እና 960 የቤት እንስሳት በጎርፍ አደጋ ተጠቅተዋል፡፡
የጎርፍ ሙላት ተከስቶባቸው በአመዛኙ ጉዳት ባደረሰባቸው ናኩሩ፣ ናይሮቢ፣ ኪሪንያጋ፣ ሆማ ቤይ እና ታና ወንዝ ተጎጂዎችን የማዳን እና የጠፉትን የመፈለግ ስራዎች በስፋት እየተሰሩ ቀጥለዋል፡፡
ትምህርት ቤቶች ከመደበኛ የማስተማር ስራቸው ተስተጓጉለዋል፡፡ የኬኒያ መንግስት በአሁኑ ወቅት አደጋውን የመከላከል ስራ እየሰራ ሲሆን፣ በተለይም 178 ግድቦች ባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች ከአካባቢው እንዲለቁ፣ ከባድ ዝናብ የመዝነብ ሂደቱ ሊቀጥል ስለሚችል መላው ኬኒያዊያን በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ጠይቋል፡፡
ይኸው ከባድ ዝናብ እና ጎርፍ አደጋ በኬኒያ ብቻ አያበቃም፡፡ ክንዱ አይሎ የምስራቅ አፍሪካ አብዛኞቹ ሀገራትን አዳርሷል፡፡ ከተጎጂ ሀገራት መካከል ቡሩንዲ ትገኝበታለች፡፡ የቡሩንዲ የሚከፋው ከባድ ዝናብ መዝነብ የጀመረው ከፈረንጆቹ አዲስ ዓመት መግቢያ ጥር ወር 2024 ጀምሮ መሆኑ ነው፡፡
እስካሁን ድረስም 179 ሺህ 200 ሰዎች በጎርፍ አደጋ ቀጥተኛ ተጎጂዎች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 31 ሺህ 200 ሰዎች ጨርቄን ማቄን ሳይሉ ቤታቸውን ትተው ለመሰደድ በቅተዋል፡፡ የሀገሪቱ 80 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች መተዳደሪያቸው ግብርና እና ተያያዥ እንቅስቃሴዎች ናቸው፡፡
የሀገሪቱ የምግብ ዘርፍ መረጃ እንደሚያመለክተውም፣ በቤተሰብ ደረጃ 23 ሺህ 109 የሚሆኑት፣ ሰብል የሚያመርቱበትን ማሳ በጎርፍ ሙላት ምክንያት አጥተዋል፡፡ ወደ 40 ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱ በምርት ዓመቱ ለማምረት ካሰበችው መሬት 10 በመቶ የሚሸፍን ነው፡፡
ከፍተኛ የዝናብ መጠን መመዝገቡ የጎርፍ ሙላት ከማስከተሉም በላይ ግዙፉ የታንጋኒካ ሃይቅ ሞልቶ ጉዳት እንዲያደርስ ምክንያት ሆኗል፡፡ አደጋው ባለፈው ዓመት በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሌራ በሽታ እንዳስፋፋም ተነግሯል፡፡
የቡሩንዲ ጎረቤት የሆነችው ሩዋንዳም ሌላኛዋ ተጎጂ ሀገር ናት፡፡ በሩዋንዳ ከሚያዚያ 28 እስከ ግንቦት 2/ 2024 ድረስ፣ ከባድ ዝናብ ባስከተለው የጎርፍ አደጋ በንያንዛ ወረዳ 14 ሰዎች ለሕልፈት ሲዳረጉ፣ በቡሬራ ወረዳ 27 ሰዎች ቆስለዋል፡፡ መንገዶች እና ድልድዮች ወድመዋል፡፡ 123 ቤቶች እንዳልነበሩ ሆነዋል።
ሩሃንጎ በተባለው ወረዳ ሰፊ ሄክታር የሚሸፍን ሩዝ አና ሙዝ የተመረተበት ማሳ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡
የሀገሪቱ ሚቲዎሮሎጂ ድርጅት ይፋ እንዳደረገው ከ40 እስከ 50 ሚሊ ሜትር የሚጠጋ መብረቅ የቀላቀለ ከባድ ዝናብ በመዝነቡ፣ በሀገሪቱ ሰሜን፣ ምዕራብ እና ደቡብ ክልሎች በሚገኙ 17 ወረዳዎች ላይ ጉዳት አድርሷል፡፡ በአንዳንድ ወረዳዎች ደግሞ እስከ 105 ሚሊ ሜትር የሚጠጋ የዝናብ መጠን ተመዝግቧል፡፡
ሌላኛዋ ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ታንዛኒያም ከዚሁ አደጋ አላመለጠችም። በታንዛኒያ ሚያዚያ 7/ 2024 በጣለው ከባድ ዝናብ፣ በፕዋኒ ክልል በሚገኙት ሩፊጂ እና ኪቢቲ ወረዳዎች ብዙ መንደሮች በውሃ ተጥለቅልቀው ታይተዋል፡፡
ከሀገሪቱ የወጡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በሩፊጂ ወረዳ 25፣ እንዲሁም በኪቢቲ ወረዳ 10 መንደሮች የጎርፍ ሙላት አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት በሕይወት እና በንብረት ላይ አደጋ ደርሷል፡፡
በአጠቃላይ 125 ሺህ 670 ሰዎች በአደጋው ቀጥተኛ ተጎጂዎች ሆነዋል፡፡ በሁለት ወረዳዎች ብቻ 10 ትምህርት ቤቶች ተዘግተዋል፡፡
ከባድ ዝናብ እና የጎርፍ አደጋ በራቸውን ካንኳኳባቸው ሀገራት መካከል ጎረቤታችን ሶማሊያ ትጠቀሳለች፡፡
ከሚያዚያ 19/ 2024 ጀምሮ በጣለው ዝናብ በሰባት ወረዳዎች 127 ሺህ ሰዎች ተጎጂዎች ሆነዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል 8 ሺህ 376 ሰዎች ከቤታቸው ሲፈናቀሉ፣ 7 ሕጻናት ለሕልፈት ተዳርገዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት እንዳመለከተው፣ በኬኒያ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ እና ሌሎች የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ከባድ ዝናብ ጥሎ በተከሰተ የጎርፍ አደጋ 637 ሺህ ሰዎች ተጎጂዎች ሆነዋል። ከእነዚህም መካከል 234 ሺህ ሰዎች ከገዛ ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ሪፖርቱ በቀጥታ ኢትዮጵያን አያካትት እንጂ በሀገሪቱ በተለይም በሚያዚያ ወር በአብዛኞቹ አካባቢዎች ተከታታይነት ያለው ከባድ ዝናብ መዝነቡ ይታወሳል፡፡ ይፋዊ መረጃ አይውጣ እንጂ በአንዳንድ አካባቢዎች በሰው እና በንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰ የጎርፍ አደጋ ተከስቷል፡፡
የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት እንዳመለከተው፣ በሚቀጥሉት ቀናት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ዝናብ ሊመዘገብ እንደሚችል ተንብዩዋል፡፡
ታዲያ በዚህ ወቅት ምስራቅ አፍሪካን የወጠረው ይህ የአየር ሁኔታ፣ ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር እንደሚያያዝ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በዋናነትም በሕንድ ውቅያኖስ ምዕራባዊ ክፍል ከተለመደው ውጪ ሙቀት ሲስተናገድ እና ኤልኒኖ የተሰኘው የአየር ለውጥ ሲከሰት፣ ምስራቃዊው የአፍሪካ ክፍል ላይ ከባድ ዝናብ ይዘንባል፡፡
ይህ የዝናብ መጠንም ከዚህ ቀደም ከሚዘንበው ከአማካይ መጠን 300 በመቶ ብልጫ አለው፡፡ ለዚህ ነው እንደ ኬኒያ፣ ሶማሊያ፣ ኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ታንዛኒያ፣ ዩጋንዳ እና ደቡብ ሱዳን ባሉ ሀገራት አደገኛ ጎርፍ የሚከሰተው፡፡
ለማንኛውም አሁን በቀጠናው እየዘነበ ያለው ዝናብ ተጠናክሮ በቀጣይ ቀናት ከ200 ሚሊ ሊትር በላይ ሊመዘገብ እንደሚችል ተተንብዩዋል፡፡ ይህ የዝናብ ወቅት ማብቂያው መቼ እንደሆነ በይፋ የገለጸ አካል የለም፡፡
More Stories
በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የሚባክነውን የህዝብና የመንግሥት ሀብት ማዳን መቻሉ ተገለጸ
ቅንጅታዊ አሠራርን በማስፈን ጥምር ደን መጠበቅ፣ ማስፋትና መጠቀም እንደሚገባ ተጠቆመ
የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በማዘመን የዘርፉን ውጤታማነት ይበልጥ ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ