ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን በማጋለጥ ረገድ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ

ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን በማጋለጥ ረገድ ሁሉም ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ተገለጸ

የኮሬ ዞን ፐብልክ ሰርቪስና የሰው ሀብት መመሪያ የሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ የማጣራት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሬ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ታረቀኝ በቀለ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃ በማቅረብ የሚፈጸሙ ቅጥሮች፣ የሥራ ዕድገትና የደመወዝ ጭማሪ በሃገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያመጡት ቀውስ ቀላል ባለመሆኑ ሁሉም ባለድርሻዎች ርብርብ በማድረግ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን ማጋለጥ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎች ከእያንዳንዱ ማህበራዊ መሠረት እየተፈተሸ የሚወጣበትና የሚመለከተው አካል ግንዛቤ አግኝቶ ከዚህ በፊት የነበሩ ማነቆዎችን በጋራ በመቀናጀት የምንፈታበት መድረክ እንደሆነ አቶ ታረቀኝ ጠቁመዋል፡፡

የኮሬ ዞን ማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደለ አሸናፊ፤ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ የመንግስት ሠራተኞችና ተሿሚዎች በዕውቀት፣ በክህሎት፣ በአመለካከትና በመልካም ስነ-ምግባር በተመደቡበት ሥራ በትጋትና በጥራት መፈጸም የሚችሉት በትክክለኛ ተቋም ሲማሩና ማስረጃ ሲኖራቸው ብቻ ነው ብለዋል።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል አቶ አሰፋ አለማየሁ፣ አቶ መልካሙ አስፋው እና ሌሎችም በሰጡት ሀሳብ ሐሰተኛ የትምህርት ማስረጃዎችን የማጣራት ሥራው ካለፈው በተሻለ መልኩ ትኩረት ተሰጥቶት ከተሠራ የሚባክን የመንግስትም ሆነ የህዝብ ሃብት አይኖርም ነዉ ያሉት።

በመድረኩ ላይ የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ሂደት በተመለከተ ሰነድ የቀረበ ሲሆን ከተሳታፊዎች ጥያቄዎች እና አስተያየቶች ተነስተው ከሚመለከታቸው አካላት ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ለምለም ኦርሳ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን