የኢትዮጵያ ሉአላዊ አንድነት በማፅናት ልማቷን ለማስቀጠል ገንቢ በሆኑ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ምሁራን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

የኢትዮጵያ ሉአላዊ አንድነት በማፅናት ልማቷን ለማስቀጠል ገንቢ በሆኑ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ምሁራን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተጠቆመ

ሀዋሳ፡ ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የኢትዮጵያ ሉአላዊ አንድነት በማፅናት ልማቷን ለማስቀጠል ገንቢ በሆኑ አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ምሁራን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል አስገነዘቡ።

ዩኒቨርስቲው “ትርክቶችና ቅራኔዎች እንዲሁም መፍትሄዎቻቸው” በሚል ርዕስ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በውይይት መድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የወልቂጤ ዩንቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፋሪስ ደሊል በተዛቡ ትርክቶች ምክንያት ኢትዮጵያ ብዙ ተጎድታለች ነው ያሉት።

በዋናነት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ከዚህ ቀደም የነበሩና አንድነትን የሚያጠናክሩ ቱባ እሴቶች በእነዚህ የተዛቡ ትርክቶች ምክንያት ተንደዋል ነው ያሉት።

በመሆኑም የኢትዮጵያን ሉአላዊ አንድነቷን በማጽናት ዲሞክራሲ የሰፈነባት ሃገር ከማድረግ በተጨማሪ ልማቷን ለማስቀጠል ገንቢና አሰባሳቢ ትርክቶች ላይ ምሁራን በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ዶ/ር ፋሪስ አስገንዝበዋል።

ትርክቶችና ቅራኔዎች እንዲሁም መፍትሄዎቻቸው ላይ ያተኮረ የውይይት ሰነድ ያቀረቡት በኢትዮጵያ በሰላምና ግጭት ዙሪያ ምርምር የሚያደርጉት ዶክተር ታደሰ ብሩ የተዛቡ ትርክቶች በባህሪያቸው አስታራቂና አንድነትን የሚሸረሽሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የፓለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ ማህበረሰቡ ከባለፈው ታሪካችን ጠቃሚዎችን በመውሰድ ለሃገር በሚጠቅሙ መፍትሄዎች ላይ ማትኮር ይገባል ብለዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንዳሉት ከታሪክ አንጻር የትርክቶች መሰረታዊ ስሪታቸው ማወቅ ተገቢ ነው።

በዋናነትም በኢትዮጵያ የተዛቡና አንድነትን የሚሸረሽሩ ትርክቶች በማስተካከል ለትውልድ የተሻለች ሃገር ለማስረከብ በሚደረገው ጥረት እንደ ምሁር የድርሻቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን