የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፋይናንስ ቢሮ ከፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴር እና ከክልሉ አመራር አካዳሚ ጋር በመተባበር በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ ለኦዲት ባለሙያዎች ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ፋይናንስ ቢሮ ከፌደራል ገንዘብ ሚኒስቴርና ከክልሉ አመራር አካዳሚ ጋር በመተባበር በመንግስት ፋይናንስ አስተዳደር ዙሪያ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከክልሉ ከሁሉም መዋቅሮች ለተውጣጡ ለኦዲት ባለሙያዎች ለ15 ተከታታይ ቀናት በሆሳዕና ከተማ እየተሰጠ የነበረው የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጠናቋል።
ስልጠናው በዘርፉ የሚሰሩ ባለሙያዎችን አቅም በመገንባት የኦዲት ቁጥጥር ስርዓቱን ውጤታማ ለማድረግ አጋዥ ስለመሆኑ ሰልጠኞች ተናግረዋል።
የሀብት ብክነት እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከልና ከተከሰተም በማረሙ ሂደት የውስጥ ኦዲተሮች እና አመራሩ በጋራ መስራት እንዳለባቸው የክልሉ የመንግስት ፋይናንስ ቢሮ አሳስቧል።
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ዘይቱና ኢብራሂም በስልጠናው ማጠቃላያ እንደተናገሩት ክልሉ በአዲስ መልክ ሲደራጅ ከነባሩ ክልል በተለያዩ ርዕሶች እየተንከባለለ የመጣ የጥሬ ገንዘብ ብድርና ዕዳ ለስራው ተግዳሮት እንደነበር አስታውሰዋል።
ክልሉን ለዕዳ ጫና የዳረገውን መሰረታዊ ጉዳይ ለመለየት ጥናት ሲደረግ የሃብት አስተዳደር በጤናማ ሁኔታ ያለመመራት መሆኑን የሚያሳዩ ነገሮች በጥናት ውጤት ለመለየት መቻሉንም ኃላፊዋ አብራርተዋል።
በባለፉት ሁለት ዓመታት የጥናቱን ውጤት መነሻ በማድረግ ክልሉን ከእዳ ነጻ ለማድረግ በተደረገው ርብርብ ውጤት መመዝገቡን አንስተው የተገኘው ውጤት ወደ ኋላ እንዳይመለስ እና የውስጥ አስተዳደር ስርዓቱ ጤናማ እንዲሆን የዘርፉ ተዋናይ ለሆኑ የውስጥ ኦዲተሮች ስልጠና መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።
በስልጠናው መግቢያ እና መውጫ ፈተና የተሰጠ ሲሆን በዚህም ሰልጣኞች ከስልጠናው ያገኙትን የግንዛቤ ደረጃ ማወቅ ስለመቻሉም ወይዘሮ ዘይቱና አብራርተዋል።
የሀብት ብክነት እንዳይከሰት አስቀድሞ መከላከልና ከተከሰተም በማረሙ ሂደት የውስጥ ኦዲተሮች እና አመራሩ በጋራ መስራት እንዳለባቸውም ኃላፊዋ አሳስበዋል።
የክልሉ አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ በበኩላቸው ስልጠናው በሳይንሳዊ ስነ-ዘዴና አቀራረብ መሰጠቱን ጠቁመው፥ በቀጣይም በተግባር አፈጻጸም የሚያመጡትን ለውጥ የመለካት ስራ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አመልክተዋል።
ስልጠናው በዘርፉ የተሰማሩ የባለሙያዎችን አቅም ያጎለበተ በመሆኑ ውጤታማና ስኬታማ እንደነበርም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።
አቶ ዛዛ ጨቡ በክልሉ ፋይናንስ ቢሮ የኤች ሲ ኦ ፕሮግራም ቡድን መሪ እና አሰልጠኝ ሲሆኑ ስልጠናው ከኦዲት ሙያ ውጪ በሂሳብ ክፍያ እና ግዢ ንብረት አስተዳደር ስርዓትን እንዴት ኦዲት ማድረግ እንዳለባቸው ማወቅ እንዲችሉ እገዛ የላቀ እንደሆነም ተናግረዋል።
ስልጠናው በመግቢያ ፈተና ተጀምሮ በመውጫ ፈተና መጠቃለሉ የነበራቸውን የእውቀት ክፍተት ለመለየት ማገዙን ጠቁመው ከስልጠና በኋላ በተሰጣቸው ፈተናም የተሻለ ግንዛቤ ስለማግኘታቸው መረዳት ስለመቻሉም አንስተዋል።
አንዳንድ ሰልጣኞች በሰጡት አሰተያየት ስልጠናው የዘርፉ ባለሙያዎች የኦዲት ቁጥጥር ስርዓቱን ውጤታማ ማድረግ በሚችሉበት ደረጃ አቅም የፈጠረ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሚመደበው ውስን ሀብት ለታለመለት ዓለማ መዋል እንዲችል በየደረጃው ያሉ የፋይናንስ ተቋማት አመራር አካላት ተገቢውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸውም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
ህገወጥ የዋጋ ጭማሪ ባደረጉ የንግድ ተቋማት ላይ እርምጃ መወሰዱ ተገለጸ
የ20ኛዉ የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን ክልላዊ የማጠቃለያ ፕሮግራም በሳጃ ከተማ እደተካሄደ ነዉ
ከ120 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነባው በድርያ ባለ ስድስት ወለል ሁለገብ ህንፃ ተመረቀ