የህዝብን ሠላማዊ ግንኙነት ለማሻከር የሚሰሩ ኃይሎችን በጋራ መከላከል ይገባል- ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው
ሀዋሳ: ግንቦት 01/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የህዝብን ሠላማዊ ግንኙነት ለማሻከር የሚሰሩ ኃይሎችን በጋራ መከላከል እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ገለፁ::
ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ከቀቤና ወጣቶች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ክልሉ ቅድሚያ ሰጥቶ ከሚሰራቸው ጉዳዮች መካከል ሠላም ዋነኛው መሆኑን ጠቅሰዋል::
ቀደም ሲል በአካባቢው ተከስቶ የነበረው አይነት የፀጥታ ችግር ሊደገም የማይገባው መሆኑን ያሳሰቡት አቶ እንዳሻው የህዝብን ሠላማዊ ግንኙነት ለማሻከር የሚሰሩ ኃይሎች እንዳሉ ገልፀው እነዚህን ኃይሎች በጋራ መከላከል ያስፈልጋል ብለዋል::
ለሠላም የሚከፈለውን ማንኛውንም ዋጋ ከፍለን የህዝብን ሠላም ማስጠበቅ የኛ ድርሻ በመሆኑ ይህን እኛ እንወጣለንም ነው ያሉት:: ወጣቶችም ሠላምን በማፅናት ሂደት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጠይቀዋል::
“ከጉራጌ ወንድሞቻችሁ ጋርበሠላም ለመኖር የሚያስችሉ ሁኔታዎችን እናመቻቻለን በየደረጃው ውይይቶችም ይካሄዳሉ” ብለዋል ርእሰ መስተዳድሩ::
የውይይቱ ተሳታፊ ወጣቶች በበኩላቸው በልዩ ወረዳው ከተለያዩ መሠረተ ልማት ሥራዎች ጋርተያይዞ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን መንግስት ከሚያከናው ናቸው የልማት ሥራዎች ጎን እንደሚሰለፉ ተናግረዋል::
ወጣቱ በመደመር አስተሳሰብ ውስጣዊ አንድነቱን ማጠናከር ይኖርበታል ያሉት ደግሞ የክልሉ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ይሁን አሰፋ ናቸው::
መደማመጥ መከባበርና መተሳሰብ ያስፈልጋል ያሉት ረዳት ተጠሪው ከሌሎች ጋር ያለውን አብሮነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል::
የአዲሱ ክልል ፍሬ የሆነውን የመዋቅር ጥያቄዎችን ምላሽ ማጣጣም እንደሚያስፈልግም አስገንዝበዋል:: ይህን እድልን በመጠቀም የቀቤና ልዩ ወረዳን በሠላም በልማትና በመልካም አስተዳደር ተወዳዳሪ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል::
ይህ ትውልድ የመደመር ትውልድ በመሆኑ ከጎታች አስተሳሰቦች ተላቆ ተራማጅና ለሀገር ክብርና ልማት የሚተጋ ነው ያሉት ደግሞ የክልሉ ሠላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ካሳ ናቸው::
ሃላፊው ወጣቶች በመድረኩ ገንቢ ሀሳብ ማንሳታቸውን ገልፀው በአካባቢያቸው ሠላም ላይ ግንባር ቀደም ሚና እንዲጫወቱ ጠይቀዋል::
በውይይት መድረኩ ወጣቶቹ ያነሷቸውን የልማት ጥያቄዎችን በመያዝ ተራ በተራ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራበት ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው ለወጣቶቹ ገልፀውላቸዋል::
ዘጋቢ ፡ ማሬ ቃጦ
More Stories
የክልሉ መንግስት ከምን ጊዜም በላይ ህዝቡን ለማገልገል ዝግጁ ነው -ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
የጎፋ ዞን ሕዝብ ምክር ቤት 4ኛ ዙር መርሃ-ግብር 12ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል
ከ19ሺህ በላይ ወጣቶች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው ወደ ተግባር መግባታቸውን ተገለጸ