በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መቀነስ በሚያስችል መልኩ የማህበረሰብ ውይይቶች ተጠናክረው መቀጠላቸውን በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ገለጸ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን መቀነስ በሚያስችል መልኩ የማህበረሰብ ውይይቶች ተጠናክሮ መቀጠላቸውን በሀዲያ ዞን የሌሞ ወረዳ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ጽ/ቤት ገልጿል።

የሴት ልጅ ግርዛት ያለ ዕድሜ ጋብቻ እና ሌሎች ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ጉዳቶች በመረዳት ሌሎችን ለማስተማር ዝግጁ መሆናቸውንም የወረዳው ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በወረዳው በተለያዩ ቀበሌያት የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዳሉት፤ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች በአብዛኛው በሴቶች እና የህጻናት ጤና ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትሉ በመሆናቸው ድርጊቱን ለማስቀረት በሚያስችል መልኩ በየአካባቢያቸው የማህበረሰብ ውይይት እያካሄዱ ይገኛሉ።

የሴት ልጅ ግርዛትን ያለዕድሜ ጋብቻንና የቤት ውስጥ ወሊድን መከላከልና ማስቀረት እንዲሁም በህፃናት ላይ የሚፈጸሙ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመቀነስ እንደየአካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር በየ 15 ቀኑ የቡድን ውይይቶችን እያደረጉ በመሆናቸው ለውጦች እየመጡ መሆናቸውንም ተናግረዋል።

የሴት ልጅ ግርዛት የሚያስከትለውን ችግር በውል በመረዳት ላለመገረዝ  ወስነው ሌሎችን በማስተማር ላይ መሆናቸውን የተናገሩት ደግሞ ተማሪ ሂሩት ፍቃዱ እና ተማሪ አልማዝ ሃይሌ ናቸው።

በሌሞ ወረዳ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት የሴቶች   ንቅናቄ ተሳትፎ ማስፋፊያ ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መንግስቱ ክፍሌ እንደገለጹት፤ በወረዳዉ በሚገኙ ሁሉም ቀበሌያት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለመከላከል ከሃይማኖት ተቋማት ከዕድር መሪዎች ከሀገር ሽማግሌዎችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ይገኛል።

በወረዳ አሁንም በድብቅ የሚፈጸም የሴት ልጅ ግርዛት  መኖሩን የገለጹት አቶ መንግስቱ ድርጊቱም  የሚፈጸመው በሽታን ምክንያት በማድረግ በልምድ ገራዦች በመሆኑ ህብረተሰቡ የራሱን እና የቤተሰቡን ንጽህና በመጠበቅ በልምድ ገራዦች መታለል እንደማይገባም አሳስበዋል።

በወረዳው በሴቶች እና ህጻናት ላይ የሚፈጸሙ የኃይል ጥቃቶችንና የጉልበት ብዝበዛን ለማስቀረት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አቶ መንግስቱ ገልጸዋል።

የሌሞ ወረዳ ሴቶች እና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ጌጤነሽ አበራ በበኩላቸው ድርጊቱን ለመከላከል በሚደረገው  ርብርብ እንደ ዩኒሴፍ እና ዩ ኤን ፕ ኤፍ ኤ ያሉ አጋር ድርጅቶች ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውን ጠቅሰው በተለይ በወረዳው የማህበረሰብ ውይይት በመጀመሩ ጾታን ሳይለይ ሁሉም እንዲሳተፉ እድል የፈጠረ በመሆኑ እርስ በርስ ተሞክሮ እንዲለዋወጡ እያደረገ ይገኛል ብለዋል።

በወረዳዉ በሚገኙ ቀበሌያት 144 አመቻቾች የማህበረሰብ ውይይቱን እንዲመሩን መመደባቸውንም ወ/ሮ ጌጤነሽ ገልጸዋል።

በወረዳው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የሴቶች ክበባትን በማቋቋም ስለሴት ልጅ ግርዛት አስከፊነት ማስተማሪ የሚችሉና ሳይገረዙ እያገቡ ያሉ በርካታ ሴቶችን ማፍራት እየተቻለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

እንደ ወረዳው የሴት ልጅ ግርዛት ላይ የተሳተፉ አካላትን በህግ እስከ ማስጠየቅ ድረስ ጠንካራ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸው የተናገሩት ወ/ሮ ጌጤነሽ ማህበረሰቡም በድብቅ የሚፈጸሙ ጉጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በማጋለጥ ረገድ የበኩሉን ልወጡ ይገባል ሲሉም ተናግረዋል።

ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን