በክልሉ በመንግስትና ፓርቲ ሥራዎች የተከናወኑ አበረታች አፈፃፀሞችን በማጠናከር ለተሻለ የህዝብ ተጠቃሚነት መሥራት ይገባል – ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው

ሀዋሳ: ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በመንግስትና ፓርቲ ሥራዎች የተከናወኑ አበረታች አፈፃፀሞችን በማጠናከር ለተሻለ የህዝብ ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባ ርእሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው አሳሰቡ::

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግስትና ፓርቲ ሥራዎች የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም የግምገማ መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል::

የግምገማ መድረኩ በክልሉ የተሰሩ የመንግስትና የፓርቲ ሥራዎች አፈፃፀም ምን እንደሚመስሉ የጋራ እውቀት ለመያዝ የሚረዳ መሆኑን በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ተናግረዋል::

የእቅድ ዝግጅት፣ ፈፃሚ ማዘጋጀትና ሠራተኛን ወደ ስራ በማስገባት እንደ ክልል በፍጥነት ወደ ሥራ የተገባበት ሂደት በእጅጉ ጥሩ መሆኑንም አንስተዋል:: በሁሉም ሥራዎች ህዝብን ማሳተፍና ፍትሀዊነት ላይ የተጀመሩ ተግባራትም እንዲጠናከሩ አሳስበዋል::

የህዝብ ተጠቃሚነት ላይ የጀመርነው ሥራ አበረታች ቢሆንም ከህዝብ ፍላጎት አንፃር አሁንም ጉድለት እንዳለም አስገንዝበዋል::

የህዝብን የልማት ፍላጎት ለማወቅ ጥናት ማድረግ እንደሚገባም አንስተዋል::

እንደ ክልል የበጀት እጥረት ቢኖርም ሥራዎችን ማከናወን ተችሏል ያሉት አቶ እንዳሻው በጀት ቢኖር ደግሞ በእጥፍ መሥራት እንደሚቻል የታየበት ነው ብለዋል::

አመራሩ ለህዝብ መሥራትና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ላይ ማተኮር እንደሚገባው ያነሱት ርእሰ መስተዳድሩ፤ የአመራር አንድነትን የሚንዱ ፕሮፓጋንዳዎችን መከላከል እንደሚገባም አሳስበዋል:: የአመራር ውህደትና አንድነት ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባው እንደሆነም አሳስብዋል::

በክልሉ ያሉ መንግስታዊ አደረጃጀቶች እስከ ሰኔ ድረስ ጠንክረው መቆም እንዳለባቸው የገለፁ ሲሆን ጠንካራ አመራርና ሰራተኞችን ማበረታታት ያስፈልጋልም ብለዋል::

በሁሉም መስክ ህግ ማስከበርም ትኩረት የሚሻ መሆኑን ተናግረዋል::

ርእሰ መስተዳድሩ የ2016 እቅድ ከህዝብ ጋር ለመሥራት አግዞናል ያሉ ሲሆን በእቅድ አፈፃፀም የተመዘገበውን መልካም ጅምር መሠረት በማድረግ የቀጣይ የ2017 በጀት ዓመት እቅድ ማዘጋጀት እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጠዋል::

በ2017 በጀት አመት የሲስተም ግንባታን የሚያጠናክር፣ ወጥ የሆኑ አሰራሮችን መከተል እና ማፅናት፣ ያወጣናቸውን ደንቦች መመሪያዎችና አዋጆችን ተግባራዊ ማድረግ፣ የተጀመሩ መሰረተልማቶችን ማጠናቀቅ፣ ህዝብን በማሳተፍ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን መጀመርና በሰባቱም ማእከላት የመኖሪያ ቤት ግንባታዎች የሚጀመሩበት በመሆኑ ይህን ታሳቢ ያደረ ሊሆን እንደሚገባ አብራርተዋል::

በክልሉ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ቁርጠኝነትና መሰጠትን እንዲሁም የሚናበብ የአመራር ሥርዓትን በመከተል የተሠራበት መንገድ አበረታች መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በብልፅግና ፓርቲ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ዶ/ር ዲላሞ ኦቶሬ ናቸው::

በአመቱ የተያዘው እቅድ አሳታፊ በመሆኑና ህዝቡ ይጠቅመኛል ብሎ በማመኑ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ተሳትፎ በህዝቡ በኩል መታየቱን ገልጸዋል::

ክልሉ የተረጋጋና ሠላማዊ ይሆን ዘንድ የአመራር ውህደት በመፍጠር የተመራበት ሁኔታ ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ መሆናችንን ያመላክታል ያሉ ሲሆን ሙሉ አቅምን ከመጠቀም አንፃር ያለውን ውስንነት ማስተካከል እንዲሁም በተግባር ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮችን እያረምን መሄድ አለብን ብለዋል::

የክልሉ መንግስትና ፓርቲ ሥራዎች የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም ሪፖርት በመድረኩ የቀረበ ሲሆን በጥንካሬና በጉድለት የተለዩ ነጥቦችን በመያዝና የቀጣይ አቅጣጫን በማስቀመጥ የግምገማ መድረኩ ተጠናቋል::

ዘጋቢ፡ ማሬ ቃጦ