የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባህላዊ ዕሴቶችን መጠበቅ ወሳኝ እንደሆነ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 30/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ባህላዊ ዕሴቶችን መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን በጌዴኦ ዞን ሲካሄድ የቆየው የይቅርታና ንስሀ መርሃ-ግብር በተጠናቀቀበት ወቅት ተገለጸ።
የጌዴኦ ብሔር ሰው እርስ በርስም ሆነ ከፈጣሪ ጋር እርቅ የሚያወርድበት የይቅርታና ንስሀ ባህላዊ ክዋኔ ‹‹ፋጭኤ›› ሥርዓት ለወራት ሲያካሂድ የቆየ ሲሆን በብሔሩ ትልቅ ቦታ በሚሰጠው ካራ ሶንጎ በሚባል ባህላዊ ሥፍራ ተጠናቋል።
በተለያዩ ማህበራዊ መሠረቶች ሲደረግ ቆይቶ ለማጠቃለያ በተዘጋጀው መርሃ ግብር የተገኙት የጌዴኦ ዞን አስተዳዳሪ ዶክተር ዝናቡ ወልደ ብሔሩ ለሃገራዊ ችግሮች መፍቻነት የሚያገለግሉ የዳበረ ባህላዊ ክዋኔዎች ባለቤት እንደሆነ ገልጸው፣ በዞኑ የሚስተዋሉትን የጥላቻ ግንብ ለማፍረስ እየተደረገ ያለውን ባህላዊ እንቅስቃሴን አድንቀዋል።
ከወራት በፊት ተጀምሮ የተጠናቀቀው የዕርቅ መርሃ-ግብር ለበርካታ ዓመታት ሳይፈቱ የቆዩት ችግሮች በዘላቂነት የተፈቱበት እንደነበረ በዲላ ዩኒቨርሳቲ መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ታደሰ ክጰ ተናግረዋል።
በዞኑ፣ ሥር የሰደደው ጥላች ተነቅሎ ዕርቅ የወረደበት ስኬታማ መርሃ ግብር በመካሄዱ በእጅጉ መደሰታቸውን የገለጹት ደግሞ የባህሉ የበላይ መሪ አባገዳ ቢፎም ዋቆ ናቸው።
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ደርቤ ጅኖ በበኩላቸው፣ ይህ ችግር ፈቺ የብሔሩ ዕሴት ቅርጹንና ይዘቱን ሳይለቅ እንዲቀጥል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም አስረድተዋል።
ዘጋቢ፡ አማኑኤል ትዕግስቱ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

                
                                        
                                        
                                        
                                        
More Stories
እየተከናወነ ያለውን የኮሪደር ልማት ሥራ ከዳር ለማድረስ በሚደረገው ርብርብ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሙዱላ ከተማ አስተዳደር ገለፀ
በትምህርት ሴክተር የመረጃ አያያዝ ውጤታማነት ዙሪያ በኩረት እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
ሁሉንም የመማሪያ መጻሕፍት ባለማግኘታቸው በትምህርታቸው ላይ ጫና እየፈጠረባቸው መሆኑን በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ወረዳ የቆንጋና ቆቄ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ተናገሩ