በአለምሸት ግርማ
እንደምን ከረማችሁ ውድ አንባቢያን! የበዓል ሰሞን ነውና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቴ ይደርሳችሁ ዘንድ እየተመኘሁ ዛሬ ላጋራችሁ ወደፈለኩት ሃሳቤ ልውሰዳችሁ። የበዓል ወቅት እንደመሆኑ የዛሬው የሃሳብ አለኝ አምዴ ጉዳዬ ማጠንጠኛ ይኸው ይሆናል፡፡
ድር ድሮ በዓልን እንድንናፍቅ የሚያደርጉ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም፤ በአንድነት ተሰባስቦ ማዕድ መቋደሱ ቀዳሚው ተግባር ይመስለኛል፡፡ ዘመድ ከዘመዱ፣ ጎረቤት ከጎረቤቱ እንዲሁም ያለው ከሌለው ጋር በአንድነት ተሰባስቦ ቤት ያፈራውን የሚቋደስበት የጋራ እሴት ተጠቃሽ ነው፡፡
ይህም ኢትዮጵያዊያን በሺህ ዓመታት ታሪካችን ያዳበርናቸው እና እንደ ሙጫ ያጣበቁን የጋራ እሴቶች ባለቤት ሆነን እንድንዘልቅ አድርጎናል፡፡ ለዚህም ነው ቀደምት አባትና እናቶቻችን ኢትዮጵያዊያን ስንፈልግ አብረን የምንኖር፤ ሳንፈልግ የምንለያይ ሕዝብ አለመሆናችን ገብቷቸው በአንድነት ኖረው ለእኛ ያስረከቡት፡፡ እኔም አብሮ መኖራችን ታሪካዊ ምክንያቶች ያሉት የውዴታ ግዴታችን መሆኑን መገንዘብ ስለሚያስፈልግ/በበዓል ሰሞን የጠፋ የመሰለው አብሮነት ብቅ ስለሚል/በዛሬው የሃሳብ-አለኝ አምድ የግል ምልከታዬን ላጋራችሁ የመረጥኩት፡፡
አሰቀድመን ኢትዮጵያዊነት ታሪካዊ፣ ባሕላዊ፣ ምጣኔ ሀብታዊ፣ ፖለቲካዊ ገመዶች ያስተሣሠሩት ማንነት መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ እንደ ሃገር ከምትታወቅባቸው ጉዳዮች ዋነኛው ማንነቷን አስጠብቃ የረዘመ የሃገረ መንግሥት ግንባታ ታሪክ ማለፏ ነው፡፡ ይህም የራሷ ፊደል፣ ሥነ ሕንፃ እንዲሁም የዘመን ቀመር እንዲኖራት አስችሏል፡፡ ይህንም እንደ ትልቅ እሴት በመውሰድ አንድነትን የማጠንከሪያ ገመድ አድርጐ መውሰድ ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ አለኝ፡፡
የራሳችን ተሞክሮም ሆነ የዓለም ታሪክ እንደሚነግረን ከመነጣጠል ያተረፈ አንድም ሃገር የለም፡፡ እኛ ደግሞ በአብሮነት ገመድ የተሳሰረ እሴት ባለቤቶች ነን፡፡ በአንድ ጥላ ስር መኖራችን ግድ ስለሆነም በመተሳሰብ ላይ የቆመ ሃገራዊ አንድነት ገንብተን ዘመናትን ኖረናል፡፡ ታሪካችንን መለስ ብለን ስንቃኘው ዛሬ ላይ የደረስነው የትናንት ስህተትን በመድገም ሳይሆን በመማር መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡
ከታሪክ ሽሚያ፣ ከመጠራጠር እና ከበቀል ርቀን እሴቶቻችንን ሰላም እንዲሰፍን ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡ የሰው ልጅ እንከን አልባ ሆኖ አልተፈጠረም፤ ሁል ጊዜም የሚያድግ እና የሚጐለብት ማንነት የተላበሰ ፍጡር ነው፡፡ በዚህም በየዘመኑ ያለፈው እና የሚመጣው ትውልድ የተጣመመውን እያቃና ወቅቱን የሚያንፀባርቁ እሴቶችን በመላበስ የራሱን መልካም ታሪክ እየፃፈ ሊሄድ ግድ ይላል፡፡ እሴቶቻችንን እያጐለበትን የመጣን እና በመከራም ሆነ በደስታ አንድነታችን የጠነከረ ዜጐች መሆናችንን መዘንጋት የለብንም፡፡
በኢትዮጵያ ያሉ የሃይማኖት አስተምህሮዎች ፈጣሪን መፍራትን አጉልተው የሚያስተምሩ ናቸው፡፡ ይህ አስተምሮም ሰው ሰውን እንዲያከብር መሠረት ጥሏል ብዬ አስባለሁ፡፡ ምክንያቱም በአካባቢው፣ በጎሳው የተለያየ ሰው በቤተ እምነቶች ይገናኛል፤ በባህልም ይለዋወጣል፡፡ በብሔር ቢለያይም በሃይማኖት ይገናኛል፡፡ ሌሎችም አንድነቱን የሚያጠነክሩ ዝምድናዎችን ፈጥሮ ኖሯል፡፡
ይሁን እንጂ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከእነዚህ ሃይማኖታዊ እና ማኅበረሰባዊ እሴት ያፈነገጡ እንዲሁም ሥነ ልቦናዊ ቀውሰ ውስጥ የገቡ የፖለቲካ ልሂቃን ማህበረሰቡን ሲከፋፍሉት ይስተዋላል፡፡ በፖለቲካ ልሂቃኑ ፕሮፕጋንዳም አዋቂ እና ታዋቂ ያልናቸው ሰዎች ሳይቀሩ አግላይ እና ለአንድ ወገን ብቻ ተቆርቋሪ ሆነው ሲቀርቡ ተመልክተናል እየተመለከትንም ነው፡፡
ይህም ቀደም ሲል ካነሳነው የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ያፈነገጠ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህ አይነት ሂደትም እንደ ሃገርም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ በሰላም አብሮ ለመዝለቅ መሠናክልነቱ የከፋ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡
በኢትዮጵያ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ እሴቶቻችን አንድነትን እና የሃገር ፍቅርን በማስተሣሠር ሚናቸው የላቀ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ይህ ነባራዊ ሀቅ የማይዋጥላቸው አንዳንድ ልሂቃን ግን ስንጥቅ በመፈለግ ይህን አንድነት እንዲሁም ፍቅር ሲሸረሽሩት ይስተዋላል፡፡ የዚህ እኩይ እሣቤ አቀንቃኞች ሀሳብ ገዥውን ቦታ እንዳይዝም ታሪክን በወጉ መፃፍ እና መሰነድ አስፈላጊ ነው ብዬም አምናለሁ፡፡
ጠንካራ ሀገረ-መንግስት እና ብሔራዊ ማኅበረሰብ መገንባት ከፍተኛ አስተዋይነትን ይጠይቃል፡፡ በአንድ ጀምበር የሚመጣም ሳይሆን በትውልዶች እውን የሚሆን ነው፡፡ በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያውያን የምንፈልገውን ለማሳካት ቅብብሎሹን በጥንቃቄ የሚመራ ኃላፊነት የሚሠማው ትውልድ አባል ለመሆን በትጋት መንቀሳቀስን ይጠይቃል፡፡ ኢትዮጵያዊነትንም በግልጽ መሠረት ላይ እየገነቡ መሄድ የግድ ይሆናል፡፡
ስለዚህም በፖለቲካም ሆነ በሌሎች ወሳኝ መስኮች የፊት መስመሩን የሚይዙት የኢትዮጵያዊነትን የቆየ ማንነት እና አብሮ የመኖር እሴትን በጥልቀት የተገነዘቡ መሆናቸው ሊረጋገጥ ይገባዋል እላለሁ። ምክንያቱ ደግሞ ይህን ማንነት እና እሴት የተረዳ አፈናቅል፣ ግደል፣ ጥላቻን ዝራ ከሚል አስተምህሮ የተላቀቀ አስተሣሠብን ያነገበ እንደሚሆን አያጠያይቅምና ነው፡፡
ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ሃገር የቆመችበትን መሠረት በመነቅነቅ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻን በመዝራት አብሮ ዘመናትን የተሻገረውን ማህበረሰብ በማለያየት ወደ ጥፋት መንገድ መውሰዳቸው አይቀርም፡፡ ይህ እንዳይሆን ደግሞ አንድነታችንን የሚያጎለብቱ እንደ ፋሲካ/ትንሳኤ ያሉ ሃይማኖታዊ በዓላትን ጨምሮ ሃገራዊ እሴቶቻችንን በመጠቀም የአብሮነት ገመዳችንን ማጥበቅ ያስፈልጋል፡፡
በትንሳኤው ክርስቶስ ኢየሱስ የሰውን ልጅ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከመለያየት ወደ አንድነት በማምጣት የዘላለም ሕይወት እንደሰጠ ሁሉ እኛም በዓሉን ስናከብር አንድነታችንን የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማከናወን መሆን አለበት እላለሁ፡፡
ለዚህም ቀደምት እናት አባቶቻችን ያላቸውን በማካፈል እና ተሰባስበው በመቋደስ በገነቡት አንድነት ጠላቶቻቸውን ጭምር በማሳፈር ነፃነቷ የተጠበቀ ሃገር እንዳስረከቡን ሁሉ፤ እኛም እየተዳከመ የመጣውን እና በበዓል ሰሞን በስፋት የሚታየውን የአብሮነት እሴት በማጠናከር ለሃገር አንድነት ልንጠቀምበት ይገባል እያልኩ የዛሬን አበቃሁ ሠላም ለኢትዮጵያ መልካም በዓል!
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ