የመኖሪያ ቤቶች በህግ ማዕቀፍ እንዲመሩ በማድረግ የዜጎችን ሚዛናዊ ተጠቃሚነት ለማስከበር በትኩረት እንደሚሰራ ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ የመኖሪያ ቤቶች ኪራይ ቁጥጥር አዋጅ አተገባበር ዙሪያ የግንዛቤ መፍጠሪያ የውይይት መድረክ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።

የሀዲያ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ተሾመ አናሞ እንደገለፁት እንደ ሀገር የወጣውን የመኖሪያ ቤቶች የአከራይ ተከራይ አዋጅ ቁጥር 1320/2016 በፀደቀ አዋጅ ላይ ውይይት በማድረግ በፈፃሚና አስፈፃሚ ደረጃ ግንዛቤ መፍጠሪያ መድረክ ነው የተካሄደው።

የመድረኩ አስፈላጊነት የመኖሪያ ቤቶች በህግ ማዕቀፍ እንዲመሩ ማድረግ ነው ያሉት ኃላፊው አዋጁ አከራይንና ተከራይን ሚዛናዊ ባደረገ መልኩ ተፈጻሚ የሚሆን ነው ብለዋል።

አዋጁ በመኖሪያ ቤቶች ላይ ብቻ ያተኮረ መሆኑን አንስተው በአፈፃፀሙ ዙሪያ እስከታችኛው መዋቅር የግንዛቤ ስራዎች ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰሩ አመላክተዋል።

ቀጣይ ማህበራትን በማደራጀትና የቁጠባ ቤቶችን በመገንባት እንዲሁም በሌሎችም አማራጮች ዜጎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ በመጠቆም።

የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅና የቤቶች ልማትና አስተዳደር ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዳንኤል ወንድሙ በበኩላቸው አዋጁ መሰረታዊ የሆነ የሰው ፍላጎት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ጠቁመው የቤት ኪራይ ስርዓት በህግ እንዲመራ ማድረግ አከራይና ተከራይ በህግ የተሳሰረ ግንኙነት እንዲኖራቸው ከማድረግም ባሻገር የአከራይና ተከራይ መብት እንዲከበር ያደርጋል ብለዋል።

አዋጁ መንግስት የሀገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ከሚሰራቸው ተግባራት አንዱ ስለመሆኑም በመጠቆም።

በማዕከላዊ ኢቶዮጵያ ክልል ይህን አዋጅ ለማስፈፀም ከተመረጡ 6 ከተሞች ሆሳዕና አንዷ መሆኗን ያነሱት አቶ ዳንኤል አዋጁ ከግንቦት ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የተገኙት የሆሳዕና ከተማ ካንቲባ አቶ ዳዊት ጡምደዶ አዋጁ በዘመናዊ አሰራር ተግባራዊ ሲደረግ ልማዳዊ የአከራይ ተከራይ ስርዓትን በማስቀረት ለከተማው የውስጥ ገቢ አጋዥ መንገድ ስለመሆኑ ገልፀዋል።

ለአዋጁ ተግባራዊነት ህብረተሰቡን ጨምሮ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አቶ ዳዊት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡን አስተያየት የህግ ማዕቀፍ የሌለው የአከራይ ተከራይ ስርዓት በህብረተሰቡ ላይ በርካታ አሉታዊ ተፅዕኖዎችን እየፈጠረ የቆየ መሆኑን አንስተው አዋጁ ተግባራዊ እንዲደረግ ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ክትትልና ቁጥጥር በተገቢው መንገድ ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።

በመድረኩም የከተማ ምክር ቤት አባላት፣ የህግ አስፈፃሚ አካላት፣ የንግዱ ማህበረሰብና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን