ሚሻ ሚሾ

በይበልጣል ጫኔ

ሚሻ ሚሾ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚዘወተር÷ የኢየሱስ ክርስቶስን ግርፋት÷ ስቃይ እና መከራ የሚያሳይ ባህላዊ ትውፊት ነው።  መነሻው ሃይማኖታዊ ነው።

መፅሐፍ እንደሚነግረን÷ ኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ተሸክሞ ከሊጦስጥራ እስከ ቀራኒዮ በተጓዘ ጊዜ÷ ሙሾ እያወጡ እና እያለቀሱ የሚከተሉት ሴቶች ነበሩ። ሚሻ ሚሾ የተሰኘው ጨዋታ ወይም ክዋኔ መነሻውም÷ እነዚያ በክርስቶስ ኢየሱስ መከራ መስቀል አዝነው ሙሾ ያወርዱ የነበሩ ሴቶች ናቸው።

ይህ የክርስቶስ ስቅለት ማስታወሻ÷ ረዥም ዘመን ተሻግሮ የመጣ ነው። ሚሻ ሚሾ ሲደርስ ለህፃናቱ ትልቅ ደስታ ይፈጥራል። ለምን ቢሉ÷ እንደ ቡሔ አሊያም የመስቀል ሆያሆዬ÷ በሚሻሚሾም አብሮነታቸው ይደምቃል። ዕድሜ ዘመናቸውን ሁሉ ሲከተላቸው የሚኖር ትዝታም÷ በዚህ መንገድ ይፈጠራል።

የሚሻሚሾ ጨዋታ ወይም ክዋኔ የሚከወነው የስቅለት ዕለት ማለዳ ነው። የጨዋታው ተሳታፊ የሚሆኑት ህፃናት እና ወጣቶች ናቸው። በአንዳንድ አካባቢዎች ወንዶች ብቻ ሲጫወቱት ቢታይም÷ የፆታ ገደብ አይደረግበትም። ወንዶችም ሴቶችም በጋራ ሊጫወቱ ይችላሉ።

ከስቅለት ዕለት ቢያንስ አንድ ሳምንት ቀደም ብለው÷ በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ታዳጊዎች እና ወጣቶች የየራሳቸውን ቡድን ይሰራሉ። በመቀጠልም በአቅራቢያቸው ወዳለ ጫካ ወርደው ዱላ ይቆርጣሉ። ዱቃቸውን ማስጌጥ እና መሸለም የቀጣይ ቀናት ተግባራቸው ነው።

በስቅለት ዕለት ማለዳ÷ ያለው አዲስ ልብስ ይለብሳል።  ካልሆነም ያለውን አጥቦ ያጌጡበታል። በመቀጠልም ያዘጋጀውን ዱላ ይዞ ማልዶ ከቤት ይወጣል። አንዱ ሌላኛውን እየጠራ ከተገናኙና በአንድ ላይ ከተሰባሰቡ በኋላ÷ በመንደሩ ውስጥ ወዳሉ ቤቶች በማቅናት ሚሻ ሚሾ ማለት ይጀምራሉ፦

“ሆ ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ

ሚሻሚሾ ሚሻሚሾ

አንድ አውራ ዶሮ

እግሩን ተሰብሮ

እሜቴ ይነሱ

ጉስጉሻውን ይዳብሱ

ስለ ስቅለቱ

ዛቅ አድርገው ከዱቄቱ”

እያሉ÷ ቤት ለቤት ይዞራሉ። የመንደሩ ነዋሪዎች ልጅ እያሉ በዚህ መንገድ አልፈዋል። ዛሬ በእግራቸው የተተኩት ታዳጊዎች ምን እንደሚፈልጉም ይገባቸዋል። እንደተባሉትም ወደ ማጀት ገብተው ጉስጉሻውን (ዱቄት ማስቀመጫውን) ይዳብሳሉ። የአቅማቸውን ያክል ዱቄት ዛቅ አድርገውም ለልጆቹ ይሰጧቸዋል። ልጆቹም መርቀው ወደሚቀጥለው ቤት ይኼዳሉ።

ልጆቹ በዚህ መንገድ የሚበቃቸውን ያክል ዱቄት ከሰበሰቡ በኋላ÷ እንደምርጫቸው አንዲት ባልቴት ቤት እንዲጋገርላቸው ይሰጣሉ። በእርግጥ እንደሁኔታው ዱቄቱን የሰበሰቡት ወጣቶች ራሳቸው የሚያበስሉበት አካባቢም አለ።

ታድያ ከየቤቱ የሰበሰቡት እህል በስሎ ቢዘጋጅም÷ ደረቅ ነውና ማባያ ይፈልጋል። ልጆቹ (ተጫዋቾቹ) ለዚህ መፍትሄ አላቸው። ተመልሰው በመንደራቸው ውስጥ ሚሻ ሚሾ እያሉ ይዞራሉ። አሁን በዱላው ፋንታ በሁለት እጆቻቸው ድንጋይ ይዘው በማጋጨት፦

“ጨው ጨው

መዋጫ መሰልቀጫ

ዘይት ዘይት

በደብረዘይት

ጨው ጨው

መዋጫ መሰልቀጫ

ሚስቴ ወልዳብኝ

አራዳ ገበያ ተጎልታብኝ”

እያሉ÷ ደሞ እንደገና ማባያ የሚሆነውን ነገር ይሰበስባሉ። ቅድሚያ የሰበሰቡትን እህል ያስጋገሩበት (የጋገሩበት) ቦታ÷ ወጡ ይሰራል። በዕለተ ስቅለት÷ የስግደቱ ስርዓት ተጠናቆ ሰዉ ከቤተ ክርስቲያን ሲመለስ÷ ሚሻ ሚሾ በተጫወቱት ልጆች አማካኝነት የመንደሩ ነዋሪ ይጠራል። “ስለ ስቅለቱ” እየተባለም÷ የተዘጋጀው ማዕድ ይቀመሳል/ ይበላል።

ሚሻ ሚሾ ተጫውተው ያመጡት ዱቄት÷ በአንዳንድ አካባቢዎች እንደ እንጀራ አነባብሮ ሆኖ ይጋገራል። ማባያውም ወጥ ተሰርቶ ይቀርባል። በሌላ ስፍራ ደግሞ የሰበሰቡት እህል ቂጣ ተጋግሮ÷ በርበሬ፣ ዘይት እና ጨው ተለውሶ ይለቃለቃል። ይህ ነው እንግዲህ÷ ለህፃናቱ እና ለመንደሩ ነዋሪዎች ቀርቦ የሚበላው።

ይህ ክዋኔ በልጆች ጨዋታ ታጅቦ ሲከወን÷ እንዲሁ የልጆች ጨዋታ ቢመስልም÷ ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም እንዳለው የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይናገራሉ። ለአብነትም፡-

ልጆቹ ሚሻሚሾ በሚጫወቱ ጊዜ ዱላ/በትር መያዛቸው÷ ኢየሱስ ክርስቶስ በአይሁዶች እጅ መመታቱን/ መገረፉን ለማስታወስ ነው። ዱላውን አዥጎርጉረው የሚያስጌጡትም እንዲሁ÷ ከግርፋቱ ብዛት የተነሳ በሰውነቱ ላይ ታትሞ የቀረውን ሰንበር ለማሰብ ነው።

ከመንደር የተሰበሰበው እህል ተቦክቶ ሳይውል ሳያድር÷ በስሎ እንዲበላ መደረጉም እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡበት ታሪክ ጋር ይተሳሰራል። እስራኤላውያን ነፃ የሚወጡበት ጊዜ ሲቃረብ በሙሴ በኩል ትዕዛዝ ተቀብለው ነበር። ይኸውም፦

የመውጣታቸው ጊዜ ስለደረሰ እህል ለመጋገር እስኪቦካ እንዳይጠብቁ÷ ጥራጥሬውንም በመቁላት አሊያም በማኖፈር እንዲመገቡ የሚያሳስብ ነበር።

በዚህም ምክንያት የሚበሉትን ዳቦ ወይም እንጀራ ለመጋገር እስኪቦካ አይጠብቁም ነበር። እስኪቦካ በመጠበቅ መዘግየት እንዳይመጣ በመስጋት ወዲያው አቡክተው በቶሎ ጋግረው መመገብን ልማድ አድርገው ነበር።

በኢየሱስ ክርስቶስ የስቅለት ዕለት÷ በሚሻሚሾ ጨዋታ የተሰበሰበውን እህልም÷ እስራኤላውያንን አብነት በማድረግ ሳይቦካ ጋግረው ይመገቡታል። ይህ ተግባር ለአዲስ ኪዳን ትውልድም ምሳሌነት እንዳለው ይነገራል። እስራኤላውያን በሙሴ መሪነት ከግብፅ ባርነት ነፃ እንደወጡት÷ የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ክርስቲያኖች ከጨለማ ወደ ብርሃን የተሸጋገሩበት ነው።

ይህ የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ማስታወሻ÷ ሚሻሚሾ ጨዋታ ከጥንት ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሰ ቢሆንም÷ ዛሬ ላይ እምብዛም እየተዘወተረ አይደለም። ይህ ሃይማኖትን ከባህል አስተሳስሮ የያዘ ክዋኔ÷ አንዱ የእኛነታችን መገለጫ ነውና÷ በትኩረት መታየት እና ማደግ ቢችል ይበጃል።