በሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች በአዲሱ ስርአተ ትምህርት አተገባበር ላይ ስልጠና ተሰጠ

በቤንች ሸኮ ዞን የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ መንግሥቱ ተክለ ማሪያም በከተማው ለሚገኙ 23 የግል ቅድመ አንደኛ ትምህርት ቤቶች ለሚያስተምሩ 144 መምህራን ስልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል።

ሰልጣኞችና ተቋማት ያገኙትን ዕውቀት ወደ ተግባር በመቀየር የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልድን በመቅረፁ ስራ ላይ የበኩላቸውን ሀላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የቤንች ሸኮ ዞን የዞኑ ትምህርት መምሪያ የቀድሞ ሃላፊና የዞኑ ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ሃላፊ አቶ ግዛው ሀይሌ እንደገለፁት መንግስት በሀገሪቱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በዚህም በዞኑ የሚገኙ የግል ቅድመ መደበኛ ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች ምቹና የትምህርት ጥራትን በሚያረጋግጥ መልኩ እንዲሰሩ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ስልጠናው በአዲሱ የትምህርት ስርአት አተገባበር ዙሪያ ትኩረት አድርጎ መሰጠቱን ገልጸው በመጪው አዲስ የትምህርት ዘመን በሁሉም የግል ትምህርት ቤቶች በወጥነት ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

በተለይ ስልጠናው የትምህርት ጥራት ለማምጣት አጋዥ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በሥልጠናው የተሳተፉ መምህራን በሰጡት አስተያየት ስልጠናው ለመማር ማስተማር ስራ አቅም የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡

በመድረኩ በስልጠናው ላይ ለተሳተፉ የግል ትምህርት ቤቶች እና ሰልጣኝ መምህራን የተሳትፎ ምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም- ከሚዛን ቅርንጫፍ