ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በአሁኑ ጊዜ ለብዙዎች ህልፈት መንስኤ እየሆነ ስላለው የስትሮክ ህመም በየወቅቱ የደም ግፊት በመመርመርና የአኗኗር ስርዓትን ጤናማ በማድረግ ተጋላጭነትን መቀነስ እንደሚገባ በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነርቭ እና የጭንቅላት ስፔሻሊስት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተገኝ ሞላ ተናገሩ።
በዓለም በገዳይነት ሁለተኛ ስለሆነው ”ስትሮክ” በሽታ በማህበረሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ መሆኑ አሳሳቢነት እየጨመረ ስለመምጣቱ ገልጿል።
እንደ ዓለም ጤና ድርጀት መረጃ ከሆነ በዓለም ዙሪያ በየዓመቱ ከ15ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች በስትሮክ የሚያዙ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ 5ሚሊዮን ሰዎች ለቋሚ የአካል ጉዳት ሲዳረጉ 5ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ላይመለሱ እስከ ወዲያኛው ያሸልባሉ።
በዋቸሞ ዩኒቨርስቲ በንግስት እሌኒ መሀመድ መታሰቢያ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የነርቭ እና የጭንቅላት ስፔሻሊስትና ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር ተገኝ ሞላ ስትሮክ ያለ አንዳች ምልክት ድንገት ሊጥል የሚችል ደምፅ አልባው (silent killer) በመባል የሚታወቅ በሽታ ስለመሆኑ ተናግረዋል።
ከጠቅላላ ሰውነታችን 2በመቶ ብቻ የሚመዝነው አዕምሮችን በሰውነት ወስጥ ካለው ጠቅላላ የደም አቅርቦት ከ15 አስከ 20 በመቶ የሚሆነውን ይውስዳል ያሉት ስፔሻሊስቱ በዚህም የደም ዝውውር አዕምሮ ኦክስጅንና አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የሚያገኝ ሲሆን ይህ ሂደት ለአፍታ ሲቋረጥ ስትሮክ እንደሚከሰት አብራርተዋል።
በመሆኑም ስትሮክ የደም ስር መጥበብ፣ ሙሉ በሙሉ መዘጋት ወይንም በጭንቅላት ውስጥ የደም መፍሰስ ወደ አዕምሮ የሚሄደው ደም እንዲስተጓጎል ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልፀዋል።
የተለያዩ ዓይነት ስትሮክ ህመሞች ያሉ ሲሆን የመጀመሪያው ሚኒ ስትሮክ በአጭር ጊዜ የሚቆይ እና ሊድን የሚችል ሲሆን ሌለኛው የደም መፍሰስ እና የደም ስር መዘጋት በመባል እንደሚታወቁ ጠቁመዋል።
የህመም ምልክቶችም በድንገት ማውራት አለመቻል፣ ራስን ስቶ ለብዙ ጊዜ መቆየት የፊት መጣመም የንግግር መኮላተፍና መንቀሳቀስ አለመቻል (ፓራላይዝድ) መሆን ዋና ዋና ምልክቶች ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም የሰውነታችንን የደም ግፊት መጠን መጨመር፣ የልብ በሽታና የስኳር በሽታ ለስትሮክ ህመም የመጋለጥ ዕድል የሚጨምር በመሆኑ የአኗኗር ስርዓት ማስተካከል ጤናማ የአመጋገብ ስረዓት መከተል የአካል እንቅስቃሴ ማድረግ የበሽታውን ተጋላጭነት ይቀንሳል ነው ያሉት ስፔሻሊስቱ።
በዓለም ገዳይነት ሁለተኛ ስለሆነው የስትሮክ ህመም በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው ግንዛቤ አናሳ በመሆን በተገቢው ሊሰራበት እንደሚገባ የነርቭና ጭንቅላት ስፔሻሊስቱ አሳስበዋል።
ዘጋቢ: ሄኖስ ካሳ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
በዓሉ የብሔሮችና ብሔረሰቦችን ባህልና ፀጋዎች ለማስተዋወቅ የላቀ ሚና አለው
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ