በጎፋ ዞን የሳውላ ተልዕኮ ለትውልድ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ከ700 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ የማጋራት ፕሮግራም አድርጋለች

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 24/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ በጎፋ ዞን የሳውላ ተልዕኮ ለትውልድ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ከ700 በላይ ለሚሆኑ አቅመ ደካሞችና አረጋውያን ማዕድ የማጋራት ፕሮግራም አድርጋለች።

የጎፋ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ በበኩሉ የሃይማኖት ተቋማት ከሃይማኖታዊ ትምህርት ባሻገር የተቸገሩ ወገኖቻችን  መደገፋቸው የሚያስመሰግን መሆኑን ገልጿል፡፡

በድጋፍ ሰነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው  ንግግር ያደረጉት የሳውላ ከተማ ከንቲባ አቶ ኤርቦላ ኤርኮ በጎነት ካለን ለተቸገሩ ወገኖቻችን ማካፈል በመሆኑ ቤተ ክርስትያኗ የትንሳኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ ያከናወነችው በጎ ተግባር የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።

የጎፋ ዞን ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ጌታቸው በበኩላቸው አረጋዊያንና አቅመ ደካሞችን መርዳትና መደገፍ ከሰው ሳይሆን ከፈጣሪ  የሚገኝ ምላሽና ዋጋ ስላለው ከሃይማኖታዊ አሰተምህሮ በተጨማሪ በጎነትን ለወገኖች በማድረጋቸው  ቤተ ክርስቲያኒቱንና ምዕመኑን አመስግነዋል። 

የሳውላ ተልዕኮ ለትውልድ ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስትያን ዋና መጋቢ ሶፎንያስ ቀልብሶ ቤተ ክርስተያኗ ከሃይማኖታዊ ትምህርት ባሻገር የተቸገሩ ወገኖችን መርዳት ከፈጣሪ የተሰጠ አገልግሎት በመሆኑ የትንሳኤን በዓል ምክንያት በማድረግ  “በጎነት ለራስ ነው” በሚል መሪ ቃል ከ700 በላይ ለሚሆኑ  አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ማዕድ ማጋራታቸውን  ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ የመደጋገፍና የመረዳዳት ስራዎችን ከመንግስት ጎን በመሆን  አጠናክረን እንቀጥላለን ብለዋል፡፡

የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም አስተባባሪ የሆኑት ወ/ሮ እመቤት ዋሪ በአካባቢው የሚገኙ አቅመ ደካሞች ምንም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በዓሉን ምክንያት በማድረግ በመርዳታቸው ተደስተው በቀጣይም ይህን መሰል ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ  እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

የማዕድ ድጋፍ የተደረገላቸው አረጋውያንና አቅመ ደካሞች ቤተክርስቲያንቱና ምዕመናኑ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን