ትንሳኤ ከሞት ወደ ህይወት መነሳትን ማሳያ ብቻ አይደለም የትህትናም መገለጫ ነው – መላከ ገነት አባ ደጉዋለ አፀደ አሰፋ
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ለተከታታይ 55 ቀናት በፆም፣ በፀሎትና በስግደት እንዲሁም መልካም ተግባራት እየተናወነ የሚያልፈው ይህ ወር በተለይ የፆሙ መገባደጃ ሳምንት ለሰው ልጆች ትህትናንና ታዛዥነት በሰፊው የሚታይበት ሳምንት መሆኑን መላከ ገነት አባ ደጉዋለ ገልጸዋል፡፡
“ጌታችን በዚህ እለት የደቀመዛሙርቱን እግር በማጠቡ ትህትናን፤ የይሁዳን እግር በማጠቡ ትዕግስትን ገልጧል ይኸውም አርአያነቱን ትህትናውን የገለጠ ብቻ ሳይሆን የአለምን ሀጥያት ለማጠብና ለማንፃት መምጣቱን ማሳያ ነው” በማለት ገልፀውታል፡፡
በእለተ ሐሙስ ቤተ ክርስቲያኗ ኢየሱስ ክርስቶስ በፍጹም ትህትና የሀዋሪያትን እግር በማጠብ ዝቅ ማለትን ለታናሽ መታዘዝን በሰፊው ያሳየበት ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ዕለቱ ከሰባቱ ምሥጢራት ቤተ ክርስቲያን አንዱ ምሥጢረ ቁርባን ስለመመሥረቱና ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ በማቅረቡ የሰው ልጅ ነጻነት ያገኘበት ቀንም ነው፡፡
ስርአተ ፀሎት በሰፊው የተገለፀበት መሆኑን አንስተው “በዚች እለት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ካህናቱ ስርአቱን አድርሰው የምዕመናኑን እግር በማጠብ ከጌታችን ከመድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተማርነውን ትህትናን በተግባር በማስተማር እዲሁም ምእመናኑ የተማሩትን ትህትና በተግባር በማሳየት በታላቅ ድምቀት ይከበራል” ብለዋል፡፡
“በዚች ዕለት በሰፊው የሚታየው ትህትና በየአንዳንዳችን ሕይወት ገብቶ ሰላም ትዕግስትን መተባበርን ከሁሉም በላይ ይቅርታን የምንማርበት በመሆኑ እኛም ከእየሱስ ክርስቶስ የተማርነውን በሰፊው በመግለፅ ይቅር መባባል መታገስ ራስን ዝቅ ማድረግ ትህትናን ማሳየት አለብን” በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋ፡፡
አዘጋጅ ፡ ቤተልሔም ለገሰ

More Stories
ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፍትህና የጸጥታ ዘርፍ አመራሮችና ባለሙያዎች ሚና የላቀ መሆኑ ተገለጸ
ከአየር ንብረት ተፅዕኖ ጋር እየተስተዋሉ ያሉትን ችግሮች ለመከላከል ሁሉም የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አካባቢ ጥበቃና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን አስታወቀ
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ግብርና ቢሮ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በክልሉ ለሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች ስልጠና መስጠት ጀመረ