“ለወጣቶች ስራ እንዲፈጠርላቸው ሳይሆን ስራ እንዲፈጥሩ እመክራለሁ” – አቶ ሰለሞን ወልዴ

“ለወጣቶች ስራ እንዲፈጠርላቸው ሳይሆን ስራ እንዲፈጥሩ እመክራለሁ” – አቶ ሰለሞን ወልዴ

በደረሰ አስፋው

በልጅነት ዕድሜያቸው ነበር ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት፡፡ ከትምህርት በኋላ ግን አይዞህ የሚላቸው አልነበረም፡፡ ይሁንና አፍላ የወጣትነት እድሜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ ሊያሳልፉት አልፈቀዱም፡፡ እጅ ካልቦዘነ ስራ አይጠፋም አሉ፡፡ ከስራ ጠባቂነት ወደ ስራ ፈጣሪነት ተሸጋገሩ፡፡ የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ሀብት ለመፍጠር፡፡ የመጀመሪያ ስራቸውም አናጺነት ነበር፡፡ ከጓደኛቸው ጋር ቀረብ በማለት ሙያውን ለምደው ነበር። ይህ ሙያ የክፉ ቀን መውጫ መንገድ ሆናቸው፡፡ በጉመር ወረዳ አረቅጥ ከተማና አካባቢው በመዘዋወር አቅሙ የፈቀደላቸውን ማንኛውንም ስራ ይሰሩ ነበር።

ከዕለታት በአንዱ ቀን ግን ወደ አንዱ ወዳጃቸው ጎራ ብለው የእንጨትና ብረታብረት ሙያ እንዲለምዱ ተማጸኑት፡፡ ሙያውን ለመልመድ እንጂ ክፍያን ለመጠየቅ አልነበረም፡፡ ነገር ግን ባለንብረቱ “ሙያውን ለምደህ ለኔ ጤና አትሰጥም፣ ከሰለጠንክ ለኔም ታሰጋኛለህ”  በማለት በአካባቢው ድርሽ እንዳይሉ አደረጓቸው፡፡

የግለሰቡ አባባልና አመለካከት ግን ተስፋ አላስቆረጣቸውም፡፡ እልህ የወለደው መነሳሳትም ለዛሬው ድርጅታቸው መመስረት ጥንስስ ሆነ፡፡ “የቅርብ ከምለው ሰው ይህ አይነት ንግግር መነሳቱ በአእምሮዬ እየተመላለሰ ይረብሸኛል” የሚሉት ባለታሪካችን ከዛ ንግግር በኋላ ግን በጥረታቸው ለዚህ መድረሳቸውን ነው የተናገሩት፡፡

ከምንም ተነስተው የትልቅ ድርጅት ባለቤት ሆነዋል፡፡ ውጤታማ ለመሆን የግድ ከትልቅ መጀመር ይገባል የሚል አስተሳሰብ የላቸውም፡፡ ከትንሽ ጀምሮ ማደግ እንደሚቻል እራሳቸውን አብነት አድርገው ያቀርባሉ፡፡ ሲጀምሩ ከአንድ የእንጨት መላጊያ ውጪ አልነበራቸውም፡፡

እሱንም ተማሪ እያሉ ለደብተር እና እስክርቢቶ ተብሎ ከሚሰጣቸው ላይ እየቀነሱ ባጠራቀሙት ገንዘብ መግዛታቸውን ነው የገለጹልኝ፡፡ በአንድ ወር ውስጥ ሰርተው ለገበያ ያቀረቧት አልጋ ደግሞ ለእሳቸው ልዩ ታሪክ ያላት ናት፡፡ ከስራውም ሆነ ከሰዎች ጋር አስተዋውቃቸዋለችና፡፡

አቶ ሰለሞን ወልዴ ይባላሉ፡፡ በጉመር ወረዳ አረቅጥ ከተማ ነዋሪ ናቸው፡፡ አበቴ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ልዩ ስሙ ጉቹ በሚባል መንደር ነው የተወለዱት፡፡ ከ1ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርታቸውን በአረቅጥ መለስተኛና 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተማሩት። ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ በህመም ምክንያት ከስራ እና ከተለያዩ ማህበራዊ ጉዳዮች ሁሉ ተለይተው በመኝታ ቆይተዋል። ከህመማቸው እንዳገገሙ ቀጥታ የገቡት በአናጺነት ስራ ነበር፡፡

በገጠር አካባቢ እየተዘዋወሩ በሚሰሩበት ወቅት ነበር የዛሬውን ድርጅት ለመመስረት ሀሳቡ የተጠነሰሰው፡፡ በ1992 ዓ.ም በአረቅጥ ከተማ ቤት ተከራይተው አነስተኛ የእንጨት ስራ ላይ ተሰማሩ፡፡ በ1999 ዓ.ም በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ከ12 ጓደኞቻቸው ጋር ተደራጅተው “በእሱ ፈቃድ የእንጨትና ብረታ ብረት ስራ ማህበር” በሚል ወደ ስራ ገቡ፡፡ በሂደት የአባላቱ ቁጥር ሲመናመን እሳቸው ግን በዚሁ ስራ ለብቻቸው ቀጠሉ፡፡

ወቅቱንም እንደዚህ ያስታውሱታል፡-

“ከዚህ ቀደም ቤተሰብ ደብተርና እስክርቢቶ ብሎ ከሚሰጠኝ የቆጠብኩት ብር ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአናጺነት ስራ ያጠራቀምኩት 5 ሺህ ብር በእጄ ነበር፡፡ በዚህ ብርም የእንጨት መላጊያ በ700 ብር ገዛሁ። የተሻለ ሙያ ያለውን ግለሰብ ቀጠርኩ። ቤት ተከራይቼ ወደ ስራ ገባሁ፡፡ እንዲህ እያልኩ ሙያውን ወደ መልመድ ተሸጋገርኩ፡፡ በአጭር ጊዜም ለውጦችን አመጣሁ”

በ2006 ዓ.ም  “ቲቺዳር የቤትና የቢሮ እቃዎች ማምረቻ” የሚለውን ስያሜ ሰጥተው ስራውን ቀጠሉ፡፡ ስራውን ለብቻቸው ሲጀምሩ የአቅም ችግር (የገንዘብ እጥረት) ሳያንገዳግዳቸው አልቀረም፡፡ ለስራው የሚያስፈልግ ማሽን አልነበራቸውም፡፡ ለዚህም መላ ያበጁለት ጀመር፡፡ ወደ ቅርብ ዘመድ ጠጋ ብለው ችግራቸውን አወያዩት፡፡ ግለሰቡም ይሁንታውን አልነፈጋቸውም፡፡ 30 ሺህ ብር ብድር ሰጣቸው፡፡ በዚህም የጣውላ መሰንጠቂያ ማሽን ገዙ፡፡ አንድ መኪና ጣውላም ገዙ፡፡ ይህም ስራቸውን ለመጀመር የሚያስችላቸውን መደላደል ፈጠረላቸው፡፡

በ5 ሺህ የግላቸው ብርና በ30 ሺህ ብር ብድር የጀመረው ስራቸው ዛሬ ላይ ትልቅ ድርጅት ሆኗል፡፡ ስራቸውም አድጎ ከራሳቸው አልፎ ወገንንና ሀገርን ለመጥቀም የሚያስችል እድል ፈጥረዋል፡፡ በድርጅታቸውም በእንጨት እና ብረታ ብረት ስራ ለ10 ሰዎች የስራ ዕድል ፈጥረዋል፡፡ እሳቸውም የዚሁ ስራ አካል ናቸው፡፡ “የከፋ ችግር ካላጋጠመኝ በስተቀር ከስራው አልጠፋም፡፡ ጊዜዬንም በተገቢው ነው የምጠቀመው” ነው ያሉት፡፡

“በድርጅቴ የቤትና የቢሮ እቃዎችንና የብረታ ብረት ስራዎች በሙሉ በዚሁ ድርጅት በጥራት የሚመረቱ ናቸው፡፡ ጥራት ደግሞ ምልክታችን ነው፡፡ ገበያ አባቱን ይመስላል፡፡ በጥራት ከተሰራ ገበያው ፈልጎህ ይመጣል፡፡ ከጉመር ወረዳ አልፎ ከጌቶ ወረዳ በመምጣት ስራዎችን ያዙናል፡፡ አብዛኛው ደንበኞቼም የጌቶ ወረዳ ግለሰቦችና ድርጅቶች ናቸው። ይህም ከስራዬ ጥራት የመጣ ገበያ ነው። ሰው በስራህ ጥራትና ታማኝነት ካለ በዋጋ አይደራደርም” ሲሉ ነው የተናገሩት፡፡

ስራቸው እየተላመደ ሲመጣ ገበያውም እያደገ መምጣቱን ያነሳሉ፡፡ ትዕዛዝ እየበዛ መጣ፡፡ ይህንንም የገበያ ዕድል መጠቀም ስለሚገባ የብድር ተቋማትን በር እንዲያንኳኩ አደረጋቸው፡፡ ለዚህም ጎራ ያሉት ወደ ኦሞ ባንክ ነው፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ 50 ሺህ ብር፣ በ2ኛው 100 ሺህ፣ በ3ኛው ዙር ደግሞ 150 ሺህ ብር ብድር በመውሰድ ስራቸውን አስፋፉ፡፡ ይህንንም ብድር በወቅቱ መመለስ እንደቻሉ ነው የሚገልጹት፡፡

አቶ ሰለሞን ወደፊት አሁን ያለውን ድርጅታቸውን ለማሳደግ ወጥነዋል፡፡ ለዚህም አዋጭ የሆኑ የስራ ዘርፎችንም እያጠኑ ነው። ሌሎች ባለሙያዎችንም እያማከሩ ነው። የሆቴል ዘርፉም ቀልባቸውን የሳበውና አይናቸውን የጣሉበት የንግድ ዘርፍ እንደሆነ ጠቆም አድርገውኛል፡፡ ከራስ ጥቅም ባለፈ በአረቅጥ ከተማ የራሳቸውን አሻራ በማሳረፍ በከተማው የገጽታ ግንባታ ላይ የድርሻቸውን ለመወጣት ነው ዕቅዳቸው፡፡ አሁን የሚሰሩትንም ትላልቅ ማሽኖችና ግብአቶች በማሟላት የተሻለ ስራ ለመስራት እና በርካታ የሰው ሀይልም ለማሰማራት አቅደዋል፡፡

እንዲህ ሰርቶ መለወጥ እየተቻለ በርካታ የአካባቢው ሰዎች ወደ ሌላ ከተማ ለምን ይሰደዳሉ? ስንል ላነሳንላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፡-

“የአካባቢው ተወላጆች አካባቢውን ለቀው በሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪ ይሰደዳሉ፡፡ ይሁን እንጂ ሰርቶ መለወጥ በዚህም ይቻላል። ለዚህ ደግሞ የከተሞች የመሰረተ ልማት ችግር ሊፈታ ይገባል። ለትውልዱ የስራ በር ምክንያት ሊሆኑ ይገባል። የመብራት መቆራረጥ ትልቁ ተግዳሮት ሆኗል። አብዛኛውን ጊዜ የምንሰራው በጀነሬተር ነው። ይህም ተጨማሪ ወጪን ይጠይቃል።  በዚህና ሌሎች መሰል ችግሮች ምክንያት ከኔ ጋር የነበሩ በርካታ ልጆች ወደ አዲስ አበባ ሄደዋል፡፡ ይህም ለስደት ምክንያት ሆነዋል። በርካቶች ከስራ ውጪ እየሆኑ ላልተፈለገ ሱስ ይጋለጣሉ፡፡ የወጣትነት ጉልበታቸው ሲባክን ይታያል፡፡ ይህ አስቀድሞ መስተካከል ይገባል። እኔ እዚህ ደረጃ ስደርስ ነገሮች ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ ይህ ችግር መስተካከል አለበት” ነው ያሉት፡፡

“በዚህ ስራ መሰማራቴ በርካታ ጥቅሞችን አስገኝቶልኛል፡፡ የስራ ቦታዬም ሆነ መኖሪያ ቤቴ በኪራይ ነበር፡፡ ከኪራይ ወጥቼ በራሴ ቦታ መስራት ችያለሁ፡፡ ዘመናዊ ቤትም ገንብቻለሁ፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የፈሰሰበት ነው፡፡ ሌላም ተጨማሪ ቤት አለኝ። ለስራ የሚያስፈልጉ ትላልቅ ማሽኖች ባለቤት ሆኛለሁ፡፡ ብድር ከሚለው አስተሳሰብ ወጥቼ በራሴ ጥሪት ነው የምንቀሳቀሰው፡፡ ትዳር መስርቼ 4 ልጆችን አፍርቻለሁ፡፡ እነዚህንም በተገቢው አስተምራለሁ፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ካፒታል አፍርቻለሁ፡፡ ለዚህ ሁሉ የበቃሁት ጠንክሬ በመስራቴ፣ ጊዜዬን በተገቢው በመጠቀሜና የገንዘብ አጠቃቀሜን በዕቅድ በመምራቴ ነው” ብለዋል፡፡

“የሰው ልጅ ታላቅነት የሚገለጸው በሚያገኘው ነገር ሳይሆን ለማግኘት በሚያሳየው ጽናት ነው” እንዳለው እውቁ ምሁር (ፕለቶ) ባለታሪካችን በጉመር ወረዳ አረቅጥ ከተማ ላይ ባመጡት ለውጥ ከበሬታን አትርፈዋል፡፡ የስኬታቸው ምንጭም ጽናት መሆኑን ብዙዎች ሲገልጹ ሰማሁ። ለሌሎች ሰዎችም መነቃቃትን በመፍጠር በአካባቢ ሰርቶ መለወጥ ይቻላል የሚለውን አስተሳሰብም ፈጥረዋል፡፡

በመጨረሻም አቶ ሰለሞን ለወጣቶች መልዕክት አለኝ ይላሉ፡-

“ለወጣቶች ስራ እንዲፈጠርላቸው ሳይሆን ስራ እንዲፈጥሩ እመክራለሁ። ህልማቸውን ትልቅ ማድረግ ይገባል። የሚፈጠሩ አጋጣሚዎችን መጠቀም ይገባል እንጂ በሆነ ባልሆነ ነገር የወጣትነት አቅምንና እውቀትን ማባከን አይገባም” ነው ያሉት፡፡