ለትንሳኤ በዓል የእርድ እንስሳትና ሌሎች የበዓል ፍጆታ ዕቃዎች በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ ረገድ የተረጋጋ  ነው – በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ ሸማቾችና ነጋዴዎች

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ለትንሳኤ በዓል የእርድ እንስሳትና ሌሎች የበዓል ፍጆታ ዕቃዎች በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ ረገድ የተረጋጋ መሆኑን በጎፋ ዞን የሳውላ ከተማ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገለጹ፡፡

በጎፋ ዞን ሳውላ ገበያ የአንድ በሬ ዋጋ ዝቅተኛው 40 ሺህ ሲሆን ከፍተኛው እስከ 120 ሺህ ብር እንደሚደርስ እና ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በአቅርቦትም ሆነ በዋጋ ረገድ መረጋጋት እንዳለ ሸማቾችና ነጋዴዎች ገልጸዋል።

ለእርድ የደረሰ የአንድ ፍየል ዋጋ ዝቅተኛው 5 ሺህ ብር ሲሆን ከፍተኛው ደግሞ እስከ 20 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝና ከአምናው ጋር ሲነጻጸር የፍየል ዋጋ የተሻለ መሆኑን ሸማቾች ተናግረዋል፡፡

እንደ ሸማቾች ገለጻ የአንድ መለሰተኛ ዶሮ ዋጋ እስከ 6 መቶ ብር ትልቅ ዶሮ ደግሞ 1 ሺህ ብር  እየተሸጠ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን በአቅርቦት ረገድ የተሻለ መሆኑን  ነጋዴዎችና ሸማቾች ገልጸዋል።

አንድ እንቁላል 13 ብር በመሸጥ ላይ ሲሆን ከአምናው ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ መታየቱን ሸማቾችና ነጋደዎች አመላክተዋል፡፡

አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት እንደ ጥራት ደረጃው ከ40 ብር እስከ 75 ብር እየተሸጠ መሆኑን ሸማቾችና ነጋደዎች ተናግረዋል፡፡

ነጭ ሽንኩርት 1ኪሎ ግራም በ250 ብር እየተሸጠ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል።

ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን