ከተሞችን በማስፋፋትና የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን በማጎልበት የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በቅንጅት እንደሚሰራ ተገለፀ

ከተሞችን በማስፋፋትና የመሰረተ ልማት ተደራሽነትን በማጎልበት የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በቅንጅት እንደሚሰራ ተገለፀ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሆዶ ቡልቱማ ታዳጊ ማዘጋጃ ከተማን የማካለል መርኃ ግብር ተካሂዷል።

በመርኃ ግብሩ ላይ የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ እንጂነር ሀብታሙ በላይነህ እንደገለፁት በልዩ ወረዳው የሚገኙ በታዳጊ ማዘጋጃ የሚተዳደሩ አካባቢዎችን የውስጥ ገቢ የማመንጨት አቅም በማሳደግ ለህብረተሰቡ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በትኩረት ይሰራል።

የተለያዩ መሰረተ ልማቶችን ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን የልማት ፍላጎት ለማሟላት በቅንጅት እንደሚሰራ በመጠቆም።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊና የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ዝናቡ ዋኖሬ፤ ከተሞች በፕላን እንዲመሩና ህብረተሰቡ የከተማ ልማት ትሩፋቶችን እንዲቋደስ ለማድረግ ብሎም አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማስፋፋት ከሚደረጉ ጥረቶች የሆዶ ቡልቱማ ከተማን የማካለል ተግባር አንዱ መሆኑን ጠቁመው በቀጣይም ህብረተሰቡን በማወያየት ከተሞችን በህጋዊ ሁኔታ የማስፋፋት ስራዎች ይሰራሉ ብለዋል።

አቶ ዝናቡ አክለውም ለከተማው የወደፊት እድገት አመላካች የሆኑ ምቹ አጋጣሚዎችን በመጠቀም ህብረተሰቡ ከባለድርሻ አካላት ጎን በመሆን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በልዩ ወረዳው የሆዶ ቡልቱማ ታዳጊ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ማቴዎስ ከተማው በ2009 ዓመተ ምህረት በማዘጋጃ እንዲተዳደር መሰየሙን ጠቁመው በአሁን ጊዜ በ4 መቶ 34 ሄክታር ላይ ከተማው ተከልሎ አገልግሎት እንዲሰጥ በምክር ቤቱ ፀድቋል።

ለከተማው መጋቢ የሆኑ የዱርጊ ኦሞ ናዳን መንገድን ጨምሮ ለልማት በርካታ ምቹ አጋጣሚዎች ያሉት መሆኑንም አንስተዋል።

ምንም እንኳ ከተማው ገና ታዳጊ ቢሆንም ባለፉት ሁለት ወራት ብቻ ከግማሽ ሚሊየን ብር በላይ መሰብሰብ መቻሉን ጠቁመው በቀጣይም በከተማው የሚገኙ ሰነድ አልባ ቤቶችን በመለየት የይዞታ ማረጋገጫ በማዘጋጀትና በሌሎችም ተግባራት ከተማውን ለማልማት በትኩረት ይሰራል ብለዋል።

በፕሮራሙ ላይ የተሳተፉ የሆዶ ቡልቱማ ቀበሌ የህብረተሰብ ክፍሎችም በከተማው ህጋዊ ፕላን ወደ ስራ በመገባቱ ደስተኞች መሆናቸውን ጠቁመው በቀጣይ ከተማውን ለማሳደግ በሚደረጉ ጥረቶች የድርሻቸውን እንደሚወጡ አመላክተዋል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን