ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን

ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 22/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ያለውን የቡና ምርት በጥራትና በጥንቃቄ በማዘጋጀት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቡናና ሻይ ቅመማ ቅመም ባለስልጣን አሳሰበ።

ባለስልጣኑ በደረቅ ቡና ምርት ዝግጅትና በቅመማ ቅመም ምርት ግብይት ዙሪያ ለዞንና ለወረዳ የዘርፉ ባለሙያዎች የስልጠና መድረክ በሚዛን አማን ከተማ በማካሄድ ላይ ነው።

በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የቤንች ሸኮ ዞን ግብርና ደን አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ መምሪያ ሃላፊ አቶ መስፍን ጉብላ እንደገለፁት፤ በክልሉ ሰፊ የሆነ የቡና ሽፋን ያለው ሲሆን በዚህም ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ጥራትን ማስጠበቅ አስፈላጊ ጉዳይ ነው።

በዞኑ ያለውን የቡና ሽፋን ከማሳደግ ባለፈ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የክልሉ ቡናና ሻይ ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ በላይ ኮጁአብ እንደተናገሩት፤ ክልሉ ካለው የመሬት አቀማመጥ ጀምሮ በዙሪያው ያለው ስነ-ምህዳር ለቡናና የቅመማ ቅመም ልማት ስራ የተመቸ በመሆኑ በስፋት እየተሰራበት መሆኑን ገልጸዋል።

በክልሉ በአሁኑ ወቅት ከ560ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቡና የተሸፈነ ሲሆን ከዚህም በአጠቃላይ በየአመቱ ከ230ሺህ ቶን በላይ የቡና ምርት ይገኛል ብለዋል።

ክልሉ እንደ ሀገር እየታየ ያለውን የውጭ ምንዛሬን ዕጥረትን መቅረፍ እንዲቻልና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንዲቻል ለቡና ጥራት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት በግብረ ሀይል ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በተለይ በክልሉ ያለውን የቡና ምርት በጥራትና በጥንቃቄ በማዘጋጀት ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ባለድርሻ አካላት በቁርጠኝነት መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በስልጠና መድረኩ ላይ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተርን ጨምሮ የዞንና የወረዳ የዘርፉ ባለሙያዎች ተሳታፊዎች ሆነዋል።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን