“ሰሙነ ሕማማትና ዕለተ ትንሳኤ”

“ሰሙነ ሕማማትና ዕለተ ትንሳኤ”

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አስተምህሮ መሠረት ሰሙነ ሕማማት ከዕለተ ሆሣዕና ማግስተ ቀጥሎ እስከ ትንሣኤ ሌሊት ያለውን ቀናት የሚያጠቃልል ነው፡፡ ዕለታቱ የዓመተ ኩነኔ ወይም የዓመተ ፍዳ ምሳሌዎች መሆናቸውን ነው የእምነቱ አባቶች የሚያስረዱት፡፡ ክርስቲያኖች የክርስቶስን ውለታ እያሰቡ እጅግ የሚያዝኑበት፣ የሚያለቅሱበት፣ የሚሰግዱበት ቤት ንብረታቸውን ትተው ከሌላው ቀናትና ጊዜያት በተለየ መልኩ ቤተ ክርስቲያናቸውን የሚማጸኑበት፤ ጧት ማታ ደጅ የሚጠኑበት፤ ኃጢአታቸውን በቤተ ክርስቲያን የሚናዘዙበት በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ የሚገኝ ሳምንት መሆኑን ነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ሀገረ ስብከት የፍሰሃገነት ደብረ ሰላም ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን የስብከተ ወንጌል አገልጋይ ዲያቆን ይርጋለም አፈወርቅ የነገሩን።

ሰኞ ወይም ዕለተ ሰኑይ

እንደ እምነቱ አባቶች አስተምህሮ ይህ ዕለት አንጾሖተ ቤተ መቅደስ (የቤተ መቅደስ መንጻት)ና መርገመ በለስ የተፈጸመበት ዕለት እንደሆነ ይነገራል። (ማር.11-11፣ ማቴ.21-18-22 ሉቃ.13-6-9)፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንደፃፈው ንስሐ አልገባም አልመለስም ያለም በለሷ እንደጠወለገችና እንደተቆረጠች ሁሉ ፍሬ ባለማፍራታቸው እንደሚቆረጡ እንዲሁም ወደ እሳት እንደሚጣሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያስረዳ ነው የእምነቱ ድርሳናት የሚያስነብቡት።

ማክሰኞ ወይም ዕለተ ሠሉስ

እንደ እምነቱ ድርሳት ይህች ቀን ኢየሱስ ክርስቶስ በተናገረውና ባደረገው ላይ አይሁድ ጥያቄ ያቀረቡበት እርሱም መልስ በመስጠት ያስተማረበት ዕለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በኦርቶዶክስ ተዋህዶ የጥያቄና የትምህርት ቀን በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥያቄውም ጌታ ባደረገው አንጽሖተ ቤተ መቅደስ ምክንያት ለጸሐፍትና ፈሪሳውያን ይኸውም ትምህርት ማስተማር፣ ተአምራት ማድረግ፣ በማን ሥልጣን ታደርጋለህ? ይህንስ ሥልጣን ማን ሰጠህ?» ብለው ጠይቀውታል። (ማቴ.21-23-27)፡፡

እሮብ ወይም ዕለተ ረቡዕ

የእምነቱ አባቶች መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ በማድረግ እንደሚገልፁት ይህ ዕለት ከ12 ደቀ መዛሙርት አንዱ የሆነው የአስቆሮቱ ይሁዳ የገንዘብ ፍቅር የገነነበትና ሌባ ስለነበር በ30 ብር ኢየሱስ ክርስቶስን አሳልፎ ለመስጠት የተስማማበትና ድብቅ ሴራ ያሴረበት ነው።ይህ ብቻ አይደለም፤ አንዲት ሴት በጣም ውድ የሆነውን የአልባስጥሮስ ሽቱ በኢየሱስ እግር ሰብራ ስታፈስ ተሽጦ ገንዘቡ ለደሆች ቢሰጣቸው ብሎ ለገንዘብ ያለውን ፍቅር በአደባባይ ያስመሰከረበት ዕለትም ነው ዕለተ ረቡዕ። የአይሁድ ሊቃነ ካህናትና ጸሐፍት ጌታን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ምክክር የጀመሩበት ቀን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሀይማኖት አስተምህሮ መሠረት ዕለቱ” የምክክር ቀን” በመባል ይጠራል፡፡” መልካም መዓዛ ያለው” ና “የእንባ”ቀንም ይባላል። ምክንያቱም ማርያም ዋጋው ብዙ የሆነ ሽቶ ጌታችንን በመቀባታና ስለ ሀጥያቷ ስቅስቅ ብላ በማልቀሷ ይህንን ስያሜ ተሰጠ። ማቴ 26፦3-13 ማር 14፦ 1-11 ሉቃ 22፦3-6

ሐሙስ ወይም ዕለተ ሐሙስ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓትና ደንብ መሠረት በሰሙነ ሕማማት ወይም በህማማት ሳንምንት ቅዳሴ የሚቀደሰው፣ፀሎተ ፍታሐት የሚደረገውና ፀሎተ አስተሥርዮም የሚደረገው በዚህ ዕለት ብቻ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ተራራ ወጥቶ የፀለየበትና ለደቀ መዛሙርት ወደ ፈተና እንዳይገቡ ስለፀሎት ያስተማረበት የእምነቱ አባቶች ይናገራሉ።ትሕትና ፍቅር መታዘዝ እንዲሁም የአገልግሎትን ትርጉም ለማስረዳት የደቀ መዛሙርቱን እግር በማጠቡ ሕጽበተ ሐሙስ በመባልም እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ይናገራሉ፡፡

ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው እንካችሁ ብሉ፤ ይህ ስለ እናንተ የሚፈስ ደሜ ነው ከእርሱ ጠጡ በማለት ምሥጢረ ቁርባንን የመሠረተበት ነው።

ዓርብ ወይም ዕለተ ዐርብ

እንደ እምነቱ አባቶች አስተምህሮ ይህ ዕለት ኢየሱስ ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት ከተለያዩ መከራዎች ከማለፍም አልፎ 6666 ጊዜ የተገረፈበት ነው። የአይሁድ ካህናት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከጠዋቱ 3 ሰዓት የሰቀሉበት፣ ከሦስት ሰዓታት መስቀል ላይ ቆይታ በኃላ ነፍሱን ለአባቱ የሰጠበት ነው። (ሉቃስ 23፥44) የአይሁድ ካህናት ያለበደል ያለጥፋት ንጹሕና ጻድቅ የሆነውን ጌታ የሰቀሉበት ዕለት ነው፡፡ በዚያን ጊዜ አሳልፎ የሰጠው ይሁዳ እንደተፈረደበት አይቶ ተጸጸተ ሠላሳውንም ብር ለካህናት አለቆችና ለሽማግሎች መልሶ ንጹሕ ደም አሳልፌ በመስጠቴ በድያለሁ አለ፡፡ብሩንም በቤተ መቅደስ ጥሎ ሔደና ታንቆ ሞተ፡፡

ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሳለ 7 ነገሮችን የተናገረበት ዕለት መሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ በማድረግ የእምነቱ አባቶች ይገልፃሉ።7ቱ ” አጽርሐ መስቀል ” በመባል ይታወቃሉ። እነሱም፦

1.” አምላኬ አምላኬ ለምን ተውከኝ” ማቴ 17፦46

2.” አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው” ሉቃ. 23፦34

3.” ዛሬ በገነት ከኔ ጋር እንድትኖር በእውነት እነግርሃለሁ” ሉቃ 23፦4

4.” አባት ሆይ ነፍሴን በእጅህ አደራ እሰጣለሁ” ሉቃ 23፦ 46

5.” እነሆ ልጅሽ እነኋት እናትህ” ዮሐ 19፦26

6.” ተጠማሁ” ዮሐ 19፦28

7.” ሁሉ ተፈጸመ ” ዮሐ 19፦ 30

እንደ እምነቱ አባቶች ገለፃ ክርስቶስ ሁሉ ተፈጸመ ብሎ ስጋው በራሱ ፈቃድ ከለየ በኋላ አምላክነቱን ለመግለፅ የታዩ ተአምራት የሚከተሉት ናቸው፤

በሰማይ 3 ተአምራት ሆኑ።(ማቴ 24፦29 ና 27፦45)

1. ፀሐይ ጨለመች

2. ጨረቃ ደም ሆነች

3. ከዋክብት ረገፉ

በምድር 4 ተአምራት ሆኑ።(ማቴ 27፦51_53)

1. የቤተ መቅደስ መጋረጃ ከላይ እስከ ታች ተቀደደ

2. ምድር ተናወጠች

3. መቃብሮች ተከፈቱ

4. ሙታን ተነሱ

ቅዳሜ ወይም ቀዳሜ ስዑር

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ድርሳናት እንደሚገልፁት በዚህች ዕለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በከርሰ መቃብር ዐርፎ የዋለባት ዕለት በመሆኗ «ቀዳሜ ስዑር » ትሰኛለች፡፡ ስዑር ቀዳሜ የተባለችው በዓመት አንድ ቀን ስለ ምትጾም ነው፡፡ ምክንያቱም እናቱ ድንግል ማርያም ወዳጆቹ ቅዱሳን ሐዋርያት ጌታ ተላልፎ ከተሰጠበት ዕለት አንስተው ብርሃነ ትንሣኤውን እስኪያዩ ድረስ እህል ውኃ በአፋቸው አልዞረም፡፡ ይመኩበትና ተስፋ ያደረጉት የነበረ አምላካቸው በመቃብር ስላረፈ ዕለቷን ሞቱን በማሰብ ትንሣኤውን በመናፈቅ በጾም አክብረዋታል፡፡

ሰንበት ወይም ዕለተ ትንሳኤ

በዚህ ዕለት የተከናወኑ ሁነቶችን የእምነቱ አባቶች እንደሚከተለው ይገልፃሉ፦

“መግደላዊት ማርያምና ሁለተኛይቱ ማርያም ሽቱ ይዘው ማለዳ ኢየሱስ ወደተቀበረበት መቃብር የሄዱበትና እያዚያ ሲደርሱ ድንጋዩን ማን ያንከባልልልና እያሉ ተንከባሎ የኢየሱስን ከሞት መነሱቱን መልአኮች ያበሰሩበት ነዉ የሚገልፁት።

ደቀ መዛሙርቶች በኢየሱስ ሞት አዝነው ቤት ዘግተው ሳሉ ኢየሱስ ከሞት ተነስቶ በተዘጋ ቤት ሳይከፈት ገብቶ “ሠላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ የገባበት እንደሆነ ይገለፃል።(ሉቃስ 24 ፥36)

ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቶች ከሞት መነሳቱን ሰውነቱን በማሳየት ያረጋገጠበት ነው። የክርስቶስ ተከታዮች ሳያዩ በማመን እምነት መኖር የሚችሉበትንና ጥርጣሬ ከህይወታቸው ማስወገድ እንዳለባቸው ያስተማረበት ነው፡፡

የሰው ልጅ በክርስቶስ ኢየሱስ ካመነ በሥጋ ኖሮ ሞቶም ህያው ነው።ምክንያቱም የክርስቲና እምነት መሠረት የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐንስ ወንጌል 11፥25 ላይ “ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤”ይላልና።

የመረጃ ምንጮች፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ማህበረ ቅዱሳንና የእምነቱ ድርሳናት

አዘጋጅ፦ ዘርሁን ሹፌር – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን