በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በማህበርና በቡድን የተደራጁ ሴቶች በግብርና እና በንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

በጎፋ ዞን ኦይዳ ወረዳ በማህበርና በቡድን የተደራጁ ሴቶች በግብርና እና በንግድ ዘርፎች ተሰማርተው ውጤታማ መሆናቸውን ገለጹ

በሁሉም መስኮች የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የወረዳው ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት አስታውቋል።

በወረዳው በጥራጥሬ ምርት ከተሰማሩ ሴቶች መካከል ወ/ሮ ታመነች ታደሰና ወ/ሮ ሣራ መሸሻ ከመደራጀታቸው በፊት ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ መኖራቸውን አስታውሰው ሥራ ከጀመሩ ወዲህ ትርፋማ በመሆን በኑሮአቸው ላይ ለውጥ እያሳዩ መምጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

በንብ ማነብ ማህበር ከተደራጁ ሴቶች መካከል ወ/ሮ አልማዝ አማረ እንደሚሉት ሴት መሆን ለመስራት ያሰብከውን ከመስራትና ለመሆን የምትፈልገውን ለመሆን አንዳችም የሚከለክል ነገር እንደሌለ ተናግረው ከዘርፉ በሚያገኙት ገቢ ቤታቸውን እያስተዳደሩና ኑሮአቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ እየታየ መሆኑን አንስተዋል።

ከግብርና ባለሙያዎች ባገኙት ትምህርት መሰረት ንብ በማነብ የተሰማሩት ወ/ሮ ሙቁን መዜነህ ዘመናዊ የንብ ቀፎ በአግባቡ መጠቀማቸው በስራው ውጤታማ በመሆን የተሻለ የማር ምርት ለማግኘት እንዳስቻላቸው ገልጸዋል።

የኦይዳ ወረዳ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ መስከረም ወዬሳ ሴቶች የኢኮኖሚ ጥገኛ ከመሆን ተላቀው በራሳቸው አቅም በተለያዩ ገቢ በሚያስገኙ ስራዎች ላይ በመስማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት እየተሰራ ነው።

በወረዳው በ10 ማህበራትና በ318 የልማት ቡድኖች ሴቶችን በማደራጀት በንብ ማነብ ፣ በጥራጥሬ ንግድና በግብርና ዘርፍ ላይ እንዲሰሩ የድጋፍና ክትትል ስራዎች በመሰራታቸው በሴቶች ኑሮ ላይ ውጤታማ ለውጥ እየታየ ስለመምጣቱ አስረድተዋል።

ወደ ስራ የገቡ ሴቶች በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የድጋፍና ክትትል ስራዎችን አጠናክረው መቀጠላቸውን ወ/ሮ መስከረም ተናግረዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ስንታየሁ ሙላቱ – ከሳውላ ጣቢያችን