የሆሳዕና በዓል “ሆሳዕናን በሆሳዕና” በሚል መሪ ቃል በሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል

የሆሳዕና በዓል “ሆሳዕናን በሆሳዕና” በሚል መሪ ቃል በሆሳዕና ደብረ ገነት ቅድስት ማርያም ቤተክርስቲያን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች እየተከበረ ይገኛል

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 20/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ የትንሳኤ በዓል ሊከበር አንድ ሳምንት ሲቀረው በደማቅ ሁኔታ የሚከበረው የሆሳዕና በዓል “ሆሳዕናን በሆሳዕና” በሚል መሪ ቃል በታላላቅ የዕምነት አባቶች፣ ሰንበት ተማሪዎችና ምዕመናን ታጅቦ በተለያዩ ሃይማኖታዊ ስርዓቶች እየተከበረ ነው።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ መልዓከ ህይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀ እንደገለፁት በዓሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ክብሩን አዋርዶ በአህያ ውርንጭላ ላይ ሆኖ በኢየሩሳሌም ደብረ ዘይት ተራራ አቅራቢያ ከምትገኘው ቤተፋጌ የአህያ ውርንጭላ አስመጥቶ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም የሄደበትን አብነት በማድረግ የሚከበር ነው።

ኢየሱስ ክርስቶስ በውርንጭላዋ ላይ ሆኖ ሲሄድ በወቅቱ ህዝቡና የኢየሩሳሌም ህፃናት በመንገድ የዘምባባ ዝንጣፊ እያነጠፉ “ሆሳዕና በዓርያም በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” እያሉ የመዘመራቸውን የሃይማኖታዊ አስተምህሮት በመከተል መሰል ስርዓቶች እየተከናወኑ የሚከበር ስለመሆኑም ስራ አስኪያጁ አመላክተዋል።

በበዓሉም የሀዲያ፣ ስልጤ፣ ከምባታ፣ ሀላባ፣ ጠምባሮና የደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስን ጨምሮ ታላላቅ የእምነት አባቶችና ከተለያዩ አካባቢዎች በዓሉን ለመታደም የመጡ የዕምነቱ ተከታዮች በእምነቱ ስርዓት በዓሉን እያከበሩት ይገኛል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን