በክልሉ ስር በ12 ዞኖች የመምህራንና የትምህርት አመራር ሙያ ብቃት ምዘና በተሳካ ሁኔታ መሰጠቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ

በክልሉ ስር በ12 ዞኖች የመምህራንና የትምህርት አመራር ሙያ ብቃት ምዘና በተሳካ ሁኔታ መሰጠቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በክልሉ ስር በ12 ዞኖች የመምህራንና የትምህርት አመራር ሙያ ብቃት ምዘና  በተሳካ ሁኔታ መሰጠቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አስታውቋል።

የተሰጠው ምዘና ፈተና ከዚህ በፊት ተመርቀው ከወጡት የሙያ ዘርፍ ጋር የሚገናኝ ሆኖ ማግኘታቸው ተመዛኞች በበኩላቸው ገልፀዋል።

በቀጣይ ራሳቸውን አውቀውና ለተሻለ ለውጥ ተግተው ለመሥራት የሚያነሳሳ ምዘና በመሆኑ ሁሉም መምህራንና የትምህርት አመራር አካላት ምዘናውን ቢወስዱ ይጠቅማል ብለዋል።

በአሪ ዞን 199 መምህራንና የትምህርት አመራር በምዘናው ተመዝግበው መቀመጣቸውን የአሪ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ ዳግም መኮንን ገልፀዋል።

የአሁኑ በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ቢሆንም በቀጣይ ሁሉም መምህራን የሙያ ብቃት ኖሯቸው እንዲያስተምሩ የሚያስገድድ መምሪያ በቅርቡ ተዘጋጅቶ ወደ ተግባር ይገባል ተብሏል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የአጠቃላይ የትምህረት ኢንስፔክሽን ባለሙያ ወ/ሮ ቅድስት በቀለ በበኩላቸው የተሰጠው ምዘና ለትምህርት ጥራት መሻሻል አንዱ አማራጭ ነው ብለዋል።

መምህራን በራሳቸው ብቃትና ክህሎት ተመዝነው ተወዳዳሪ ዜጋን ከመፍጠር አኳያ የራሳቸውን ሀላፊነት እነዲወጡም ወ/ሮ ቅድስት አሳስበዋል።

የምዘና ሂደቱ የተሳካ እንደነበረ የገለፁት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ የመምህራንና የትምህርት አመራር ሙያ ፈቃድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ስምዖን ደስታ ናቸው።

በክልሉ ስር ባሉ 12 ዞኖች 5ሺህ 5 መቶ  59 መምህራን የትምህርት አመራር ለምዘናው ተመዝግበው መቀመጣቸውንም ሀላፊው ተናግረዋል።

ፈተናው በትምህርተ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የወረደ መሆኑንም አቶ ስምዖን ገልፀው በቀጣይ ለተመዛኙ በሀገር አቀፍ ሰርተፊኬት ይዘጋጅላቸዋል ብለዋል።

ከዚህ በፊት የተመዘኑ መምህራን ፈቃዳቸውን የሚያድሱበት ሁኔታ አለመቻመቻቸቱ በመግለጽ አሁን ላይ ተተሻሽሎ የሚያድሱበትና የተለያዩ ማትጊያዎችን ጨምሮ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች እንዲያገኙ ይደረጋል ብለዋል።

ለዚህም እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና በትምህርት ሚኒስቴር በኩል የሚሰጠውን የሙያ ብቃት ምዘና መወሰድ እንደሚጠበቅባቸው ተገልጿል።

ዘጋቢ: ተመስገን አበራ – ከጂንካ ጣቢያችን