ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ የበጎ አድራጎት ባህል ማሳደግ የሁል ጊዜ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ የበጎ አድራጎት ባህል ማሳደግ የሁል ጊዜ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሊሆን እንደሚገባ ተገለፀ

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሀዲያ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የ2018 ዓ.ም ጠቅላላ ጉባኤ በሆሳዕና ከተማ ተካሄዷል።

አቶ ወንድሙ አበራ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር የሀዲያ ዞን ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ፥ ተቋሙ በመላው አለም የሚገኝ በሰው ልጆች መካከል ያለ ልዩነት በእኩልነት የሚረዳ ዓለም አቀፋዊ ሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ድርጅት መሆኑን አመላክተዋል።

ድርጅቱ እንደ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች በሚከሰቱ ድንገተኛ አደጋዎች ፈጥኖ በመድረስ የቁሳቁስና የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የድኃ ድኃ ቤተሰቦችን በመለየት የቤት ለቤት የህክምና ብሎም የምግብ ድጋፍ ያደርጋል ያሉት ኃላፊው፥ በመጠቆም እንደ ሀዲያ ዞን በውኃ መሠረተ ልማት ተደራሽነት የተሰሩ ስራዎች የሚበረታቱ መሆናቸውን አመላክተዋል።

አቶ ታምራት አኑሎ የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አማካሪ ቀይ መስቀል ሰብዓዊነትን መሠረት አድርጎ የሚሰራ ዓለም አቀፋዊ ገለልተኛ ተቋም መሆኑን ገልጸው፥ የብልጽግና ፓርቲ የሚያከናውናቸውን ሰው ተኮር ስራዎች ከመደገፍ አንፃር ጉሊህ አበርክቶ ያለው መሆኑን አስገንዝበዋል።

ይሁን እንጂ እንደ ተቋሙ ተልዕኮ በሚፈለገው ልክ ከመደገፍ አንፃር ክፍተቶች የሚስተዋሉ በመሆኑ ዓላማውን በመገንዘብ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ ይጠበቃል ብለዋል።

አቶ አብርሃም መጫ የሀዲያ ዞን ቀይ መስቀል ማህበር ቅርንጫፍ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ በበኩላቸው፥ እንደ ሀዲያ ዞን ተቋሙ ከተቋቋመ ወደ 32 ዓመታት ያስቆጠረ መሆኑን ጠቁመው፥ ማህበሩ በበጎ አድራጎት ላይ የተመሠረተ፥ የፋይናንስ ምንጩም የአባላት መዋጮ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር ሆነ እንደ ዞን ማህበሩን በሚፈለገው ከመደገፍ አንፃር ክፍተቶች ያሉበት በመሆኑ ይልቁንም ከታችኛው መዋቅር ጀምሮ ሊሰራበት እንደሚገባ ተናግረው፥ በቀጣይ በሁሉም መዋቅሮች አምቡላንስና መድኃኒት ቤቶችን ተደራሽ ከማድረግ አንፃር በትኩረት ይሰራል ነው ያሉት።

በመድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ቀይ መስቀል ማህበር ኃላፊ ዳንኤል አንጭሶ ዶ/ር፥ ቀይ መስቀል ማህበር ከአድሎ የፀዳ ገለልተኛ የበጎ አድራጎት ማህበር መሆኑን ጠቁመው፥ ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ የበጎ አድራጎት ባህል ማሳደግ የሁል ጊዜ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ ሊሆን ይገባል ብለዋል።

በተቋሙ የአደጋ ምላሽ መረጃን በወቅቱ ከማድረስ አንፃር በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በየአካባቢው የሚስተዋሉ የአምቡላንስ ችግሮችን ብሎም የመድኃኒት ቤት ተግዳሮቶችን ተነጋግረን ልንፈታ ይገባል ብለዋል ።

በተቋሙ አባላትን በተገቢ ከማደራጀት አንፃር ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አመላክተዋል።

በመድረኩም የክልሉ ቀይመስቀል ማህበር ኃላፊ ዳንኤል አንጭሶ ዶ/ር ጨምሮ እስከ ታችኛው መዋቅር የሚገኙ የመምሪያ ኃላፊዎችና የወረዳ ብሎም የከተማ አስተዳደሮች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን በጉባኤው የዞኑ ቀይ መስቀል ማህበር ቦርድ አባላት ምርጫ ተካሂዷል።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን