የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባርን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው – የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት

የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባርን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት አለባቸው – የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት

ሀዋሳ፡ የካቲት 06/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባርን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸው በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ትምህርት ጽህፈት ቤት ገለፀ፡፡

የልዩ ወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት የ2018 የትምህርት ዘመን የትምህርት ቤቶች የግማሽ አመት የተግባር አፈፃፀም መድረክ ከርዕሰ መምህራንና ባለድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ እያካሄደ ይገኛል፡፡

የቀቤና ልዩ ወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት ሃላፊ አቶ አህመድ ሀሰን በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ የመድረኩ ዋና አላማ በ2018 የትምህርት ዘመን በግማሽ አመቱ በትምህርት ልማት ዘርፍ የተሰሩ ጠንካራ ጎኖችንና ውስንነቶችን በመለየት በቀጣይ የተሻለ ስራ ለመስራት ያለመ ነው፡፡

በትምህርት ዘመኑ ባለፉት 6 ወራት ማህበረሰቡንና አጋር አካላትን በማሳተፍ የአቅም ውስንነት የለባቸው ተማሪዎችን በመለየት የመማሪያ ቁሳቁስ የማሟላት እንዲሁም የመቀመጫ ወንበሮች፣ የማጣቀሻና የመማሪያ መጽሐፍትን ለተማሪዎች ከማሟላት ረገድ የተሻለ ስራ መስራት ተችሏል ብለዋል፡፡

በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ በ2018 የትምህርት ዘመን ከ30 ሚሊየን ብር በላይ ሀብት በመሰብሰብ የተማሪዎችን ውጤትና ስነ-ምግባር ለማሻሻል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ለማዋል በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ያሉት አቶ አህመድ፤ በዚህም በግማሽ አመቱ ከሚጠበቀው ዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡

ያለ በቂ መጽሐፍት አቅርቦት የተማሪዎች ውጤት ማሻሻል የሚታሰብ አይደለም ያሉት ሃላፊው፤ አንድ መጽሐፉ ለአንድ ተማሪ ንቅናቄ በማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

በመድረኩ ላይ በተለይም የተማሪዎችን ውጤት በማሻሻል ረገድ በመጀመሪያው መንፈቅ አመት የተሻለ ስራ የሰሩ ትምህርት ቤቶች ተሞክሮ ቀርቦ ውይይት በማድረግ ለሌሎች የማስፋት ስራ እንደሚሰራም አስረድተዋል፡፡

የተማሪዎች ውጤትና ስነ-ምግባርን በማሻሻል የትምህርት ጥራትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንዳለባቸውም አቶ አህመድ አስገንዝበዋል፡፡

መድረኩ ለ2 ቀናት የሚቆይ ሲሆን የትምህርት ቤቶች ርዕሰ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡

ዘጋቢ፡ ጅላሉ ፈድሉ – ከወልቂጤ ጣቢያችን