ምርታማነትን ለማሻሻል የምርጥ ዘር ብዜት ሥራን በቅንጅት ማከናወን እንደሚያስፈልግ ተገለጸ
ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 18/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) ምርታማነትን ለማሻሻል የምርጥ ዘር ብዜት ሥራን በቅንጅት ማከናወን እንደሚያስፈልግ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ረዳት የመንግስት ተጠሪ፣ የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ ተናግረዋል፡፡
የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ከግብርና ቢሮ የምግብ ሥርዓት ማስተባበሪያ ፕሮግራም /FSRP/ ጋር በመተባበር ለምርጥ ዘር አባዥ /አውት ግሮወርስ/ ባለድርሻ አካላት በዘር ብዜት ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት አካሂዷል።
በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የእለቱ የክብር እንግዳና የክልሉ ረዳት የመንግስት ተጠሪ፣ የፖለቲካና የአቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ነጋ አበራ መንግስት ከዚህ ቀደም የነበሩ የኢኮኖሚ ፖሊሲዎችን በማጠናከር በሁሉም መስክ እንደየአካባቢው ሥነ ምህዳር ተስማሚ የሆኑ መሠረታዊ የግብርና ትራንስፎርሜሽን ተግባራት ዙሪያ ትኩረት አደርጎ እየተስራ ነው ብለዋል።
በአፈጻጸም ሂደት ላይ ተግዳሮት ከነበሩት ጉዳዮች መካከል የግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና አጠቃቀም ውስንነት በዋናነት ይጠቀሳል ያሉት አቶ ነጋ፤ የመፍትሄ አካል እንዲሆን የተቋቋመው የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ገና ከጅምሩ ተስፋ ሰጪ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን አመላክተዋል።
የምርጥ ዘር ድርጅቱ በራስ አገዝ ከሚያከናውናቸው ተግባራት በተጨማሪ ለአርሶ አደሮችና አልሚ ባለሀብቶች ተደራሽ በመሆን የዘር ብዜቱን ሥራ ማስፋትና ተጠቃሚነታቸውን እያረጋገጠ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አቶ እምሩ ወይሳ ናቸው፡፡
በተቋቋመበት 10 ወራት ወስጥ ድርጅቱ እያሳየ ያለው የምርጥ ዘር አቅርቦትን አጠናክሮ በማስቀጠል በ6ቱም ዞኖች በተመረጡ ዘርፎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አቶ እምሩ አክለዋል።
ዞኑ በቱሪዝም ሀብቱ ለክልሉ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የገለጹት የኮንታ ዞን ግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ማስረሻ ሀደሮ በግብርና ግብዓት አቅርቦት በኩል ከዚህ ቀደም የነበረውን ችግር ሊፈታ የሚችልና ውጤታማ ሥራ እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።
በዞኑ ኮይሻ ወርዳ በሀማካ ቀበሌ የተቋቋመው የክልሉ ምርጥ ዘር ድርጅት የጀመራቸው ተግባራት ትልቅ የሥራ እድል ከመፍጠሩም በላይ በቀጣይ ለሌሎች አጎራባች ክልሎች የተሻሻለ ምርጥ ዘር አቅራቢ በመሆን የድርሻውን ይወጣል ብለዋል አቶ ማስረሻ።
በምክክር መድረኩ ላይ የክልል ከፍተኛ አመራሮች ከ6ቱም ዞኖች የግብርና ልማት መምሪያ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎችና፣ አርሶ አደሮች፣ አልሚ ባለሀብቶችና ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ