በሀገሪቱ የዜጎችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ይበልጥ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ

በሀገሪቱ የዜጎችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ይበልጥ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሀገሪቱ የዜጎችን የስራ ፈጠራ ክህሎት ይበልጥ ለማጎልበት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንተርፕሪነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት አስታውቋል።

ኢንስቲትዩቱ በስራ ፈጠራ ንድፈ ሀሳብ ዙሪያ በቤንች ሸኮ ሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ የተለያዩ የትምህርት ተቋማትና ስራ ፈላጊ ወጣቶች የአቅም ማጎልበቻ ስልጠና ሰጥቷል።

ስልጠናው የኢትዮጵያ ኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢንስቲትዩት ከስራና ክህሎት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር የተዘጋጀ ሲሆን ለሚዛን ግብርና ኮሌጅ ለሚያስተምሩ መምህራን ለ6 ተከታታይ ቀናት ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናው ማጠናቀቂያ ላይ የተገኙት የሚዛን አማን ከተማ አሰተዳደር ምክትል ከንቲባና የስራ ክህሎት ኢንተርፕራይዝ ልማት ፅ/ቤት ሃላፊ አቶ ስንታየሁ ጋይድ እንደተናገሩት፤ መንግስት በአሁኑ ወቅት የዜጎችን የስራ ፈጠራ አቅም ለማበረታታትና ለማሳደግ ሰፊ ስራዎች እየሰራ ይገኛል።

በተለይ በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የስራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ በትኩረት መስራት ይጠበቃል ያሉት ምክትል ከንቲባው የስራ ፈጣሪዎችን ቁጥር ይበልጥ እንዲጨምር ደግሞ በየትምህርት ተቋማት ያሉ የሰው ሀይሎች ላይ በስፋት መስራት ይጠበቃል ብለዋል።

ሰልጣኝ መምህራን የወሰዱት ክህሎትን ወደ ተግባር በመቀየርና በተጓዳኝም ቢዝነስ በመጀመር የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመለወጥ ጥረት ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

በኢንተርፕርነርሽፕ ልማት ኢኒስቲትዪት አሰልጣኝና የቢዝነስ አማካሪና እንዲሁም በኢንስቲዩቱ የሊድ ፕሮጀክት የደቡብ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል አስተባባሪ የሆኑት አቶ ስንታየሁ ሽብሩ እንደገለፁት፤ ስልጠናው በዞኑ ባለፉት ሳምንታት ለተለያዩ ተቋማትና ወጣቶች የተሰጠ ሲሆን ከእነዚህም ለሚዛን ቴፒ ዩንቨርስቲና ለአማን ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና እንዲሁም በሚዛን አማን ከተማ ለሚገኙ ሴት ስራ ፈጣሪዎች ተሰጥቷል።

ስልጠናው በአካባቢው ስላለው የስራ አማራጭና ዕድሎች በስፋት በመጠቆምና ይህንንም ተጠቅመው ተጨማሪ የቢዝነስ አቅም መፍጠር በሚችልበት ጉዳዮች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠናው ትኩረት አድርጎ መስጠት ገልጸዋል።

በተለይ በሚዛን አማን ከተማ ከ400 በላይ ለሚሆኑ ስራ ፈላጊ ወጣቶች ያላቸውን ሀብትና አቅም ተጠቅመው የተሻለ ስራ ዕድል በመፍጠር ስኬታማ የቢዝነስ ሰዎች መሆን የሚያስችል ስልጠና ተሰጥቷቸዋል ነው ያሉት።

ስልጠናው እንደ ሀገር በሚቀጥሉት 5 አመታት አንድ ሚሊዮን ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለመፍጠር ግብ ተይዞ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ስንታየሁ በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተጠናክሮ እንደሚሰጥ ገልጸዋል።

በስልጠናው ላይ የተሳተፉ የኮሌጁ መምህራንም ከሁሉ ነገር በፊት የሰዎችን አዕምሮ መቀየር ዋነኛ ጉዳይ በመሆኑ የተሰጣቸው ስልጠና በቀጣይ በራሳቸው ቢዝነስን እንዴት መስራትና ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ትልቅ ቁም ነገር አግኝተንበታል ነው ያሉት።

ዘጋቢ፡ ጦያር ይማም – ከሚዛን ጣቢያችን