የዲላ ዩኒቨርሲቲ በቡና ልማት ፕሮጀክት ያዘጋጃቸውን የተመረጠ የቡና ዝሪያ ችግኝ ለአርሶ አደሮች አሰራጨ

የዲላ ዩኒቨርሲቲ በቡና ልማት ፕሮጀክት ያዘጋጃቸውን የተመረጠ የቡና ዝሪያ ችግኝ ለአርሶ አደሮች አሰራጨ

ሀዋሳ፡ ሚያዝያ 16/2016 ዓ.ም (ደሬቴድ) የዲላ ዩኒቨርሲቲ በማህበረሰብ አገልግሎት እና አጋርነት ዳይሬክቶሬት ጽ/ቤት በቡና ልማት ፕሮጀክት ያዘጋጃቸውን የተመረጠ የቡና ዝሪያ ችግኝ ለአርሶ አደሮች እያሰራጨ መሆኑን ገለጸ።

የቡና ልማት ፕሮጀክቱ በ2009 አካባቢ ተከስቶ በነበረ የውርጭና በአብዛኛው ያረጁ ቡናዎችን ለመተካት ታስቦ የተጀመረ መሆኑን ተጠቁሟል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት 1 ሚሊየን 160 ሺህ የሚጠጋ የቡና ችግኝ ከ 2ሺህ 400 በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች መሰራጨቱ የተገለጸ ሲሆን፥ በገንዘብ 11 ሚሊየን 600 ሺህ ብር የሚተመን ዋጋ እንደላው ተመላክቷል፡፡

በይርጋጨፌ ወረዳ ዱመርሶ ቀበሌ የቡና ልማት ፕሮጀክት ጣቢያ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ሚጁ፥ ወረዳው ሰፊ የቡና ምርት ያለበት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፥ ከ2014 ዓም ጀምሮ ምርቱን በብዛት እና በጥራት ለማምረት በኩታ ገጠም እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው በቡና ላይ እየሠራ ያለውን ስራ አድንቀው፥ ይህም የቡና ጥራትን ለማስጠበቅ ጉልህ ድርሻ እንዳለውና በቀጣይ የቡና ችግኝ የማፍላቱ ተግባር ወደ ኢንተርፕራይዞች የሚሸጋገር መሆኑን ተናግረዋል።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ችሮታው አየለ እንደተናገሩት፣ ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ሕይወት የሚቀይሩ ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎቶች ላይ ሳይንሳዊ የቡና ችግኝ ዝግጅት በማድረግ ለአርሶ አደሮች በማሰራጨት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፉት አምስት ዓመታት በተሠሩ የቡና ልማት ፕሮጀክት ሥራዎች በተለያዩ ማዕከሎች ላይ የተመረጡ የቡና ችግኝ የማፍላትና ሌሎች ስራዎች ውጤት እንደተገኘባቸው አስረድተዋል፡፡ በይርጋጨፌ አካባቢ ያሉ የቡና ምርጥ ዝሪያን የመለየት እና የይርጋጨፌን ቡና በዘርነት የማቅረቡ ሥራ በተቋሙ የምርምር ዘርፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ዩኒቨርሲቲው የይርጋጨፌ ቡና ምርምርና ስልጠና ማዕከልን ለመገንባት ሀገር አቀፍ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር መጀመሩንና በቅርቡ ወደስራ በመግባት ከግብ ለማድረስ ጥረት ላይ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡና ማህበር ምክትል ሰብሳቢ አቶ ዘርሁን ቃሚሶ ፣ የቡና ባለቤት የሆነው አርሶ አደርና ሀገር ተጠቃሚ እንድትሆን ከዲላ ዩኒቨርሲቲ ጋር ስምምነት ተፈራርመው እየሠሩ እንደሆነ አመላክተዋል።

የቡና ችግር ተፈትቶ ተጠቃሚነት የሚከበረው በዕውቀት ከተሠራ ነው ያሉት አቶ ዘርሁን፥ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በመተባበር ለሚገነባው የቡና ምርምር ኢንስቲትዩት፣ ማህበራቸው 10 ሚሊየን ብር መደገፉን ጠቁመዋል።

በኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስቴር የምርምርና ማህበራዊ ጉድኝት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ ዶ/ር ዱላ ቶልራ፥ ዩኒቨረሲቲዎች እምቅ ሀብቶችን ከማዘመን አንጻር ያለውን ክፍተት ለመፍታት የሚሰሩ ተቋማት መሆናቸውን ጠቁመው፥ የዲላ ዩኒቨርሲት በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በምርምር የተገኙ ሥራዎችን ወደ ሕብረተሰቡ አቅርቦ ህብረተሰቡን ለመቀየር እውቀትን ተደራሽ ከማድረግ አንጻር እየፈጸመ ያለው ተግባር የሚያስመሰግን ነው ብለዋል፡፡

አርሶ አደር ዳዊት ግዛውና ሌሎችም በሰጡት አስተያየት፣ ዩኒቨርሲቲው በቡና ልማት ዘርፍ እያቀረበ ያለው የቡና ችግኝ በመውሰድ ያረጁ ቡናዎቻቸውን ወደ አዳዲስ ዝሪያ እየቀየሩት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ከቡና ችግኝ ሥርጭቱ በተጨማሪ የቡናና እንሰት ችግኝ ተከላ መርሃ ግብርም በወረዳው ሀፉርሳ ወራቢ ቀበሌ ተካሂዷል፡፡

ዘጋቢ፡ እስራኤል ቅጣው – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን